ህዳር 29 ቀን በሀገራችን በየአመቱ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ክፍለ ከተሞች በድምቀት መከበሩን ቀጥሏል።
በሀገራችን ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በክፍለ ከተማ ደረጃ ከወዲሁ መከበር የጀመረ ሲሆን በመናህሪያ ክፍለ ከተማ ስር በሚገኙ ቀበሌያት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በዛሬው እለት በድምቀት ተከብሯል።
አቶ ክፍሌ ዋሬ የክፍለ ከተማው ዋና አስተዳዳሪ የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በህወሓት የሽብር ቡድን በሀገራችን ተጋርጦ የነበረውን የህልውና አደጋ በጋራ በመመከት እንደ ሀገር ድል እያስመዘገብን ባለንበት በአሁኑ ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በመዝመት፣ በመለገስና አካባቢን ነቅቶ በመጠበቅ የህልውና ዘመቻው አካል ለመሆን የቀረበውን ሀገር አቀፍ ጥሪ ተቀብሎ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በርካታ ስራዎች ማከናወን መቻሉን ያስታወሱት አቶ ክፍሌ የክፍለ ከተማው አስተዳደርም በከተማ ደረጃ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ1.4ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ እንዲሁም 240 ኩንታል የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ መሳተፉንም ጠቁመዋል።
አቶ ተሻለ ኡርጌሳ በሐዋሳ ከተማ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በበኩላቸው የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የህወሓት ጁንታ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን የሽብር እንቅስቃሴ ለመመከት፣ ለማክሸፍና የሀገራችንን ህልውና ለማስጠበቅ ከምን ግዜውም በላይ አንድነታቸውን ያጠናከሩበት ወሳኝ ወቅት መሆኑን ገልፀዋል።
የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 ቀን በድሬድዋ ከተማ በልዩ ድምቀት እንደሚከበርም ይጠበቃል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ህዳር/21/2014ዓም
ሐዋሳ