በብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ በ3ኛ ዙር የወጣቶች ቅጥር ዙሪያ ከአለማማጅ ድርጅቶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ጥቅምት/17/2018/ዓም/ሐዋሳ
በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የስራ ፣አሰሪና ሰራተኛ መምሪያ የብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት 3ኛ ዙር የወጣቶች ቅጥር በማስመልከት ከወጣቶች አለማማጅ ድርጅቶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጋና ኔቶ እና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የስራ አሰሪና ሰራተኛ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ በላይነሽ ገዳ በያዙት በዚህ መድረክ የቀጣሪ ድርጅቶች ባለቤቶችን ጨምሮ የከተማ እና የክፍለከተማ ባለሞያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
መንግስት የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስቀምጦ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ አጋና ኔቶ ገልፀዋል።
ከእነዚህ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ውስጥ ብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑንም ኃላፊው አክለዋል።
ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት በማሰልጠን፣ የብድርና የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት በማዘጋጀት እየሰራ ይገኛልም ብለዋል።
የስራ አጥነት ችግርን በመንግስት አቅም ብቻ መፍታት አይቻልም ያሉት አቶ አጋና በከተማችን የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለፁት።
በከተማው የሚገኙ ድርጅቶች እስካሁን ባለው የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋግጥ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን የገለፁት አቶ አጋና ኔቶ ለአልማማጅ ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የስራ አሰሪና ፣ ሰራተኛ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ በላይነሽ ገዳ በብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት በርካታ ቁጥር ያላቸው የከተማችን ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በመድረኩ ገልፀዋል።
ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እና የስራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በመንግስት በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል ያሉት የመምሪያ ኃላፊዋ የከተማው ባለሀብቶችና ኢንዱስትሪያሊስቶች ከመንግስት ጎን ሆነው ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቁመው ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ሰልጣኝ ወጣቶቹ ልምድና ብቃታቸው አድጎ ባለራዕይ ሆነው እንዲወጡ እየሰሩ እንደሚገኝ የገለፁት ወጣቶችን በማለማመድ ላይ ከሚገኙ ተቋማት መካከል በመድረኩ እድል ወስደው ሀሳብ የሰጡ ባለሀብቶች የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የትምህርት ደረጃቸው ከ12ኛ ክፍል በታች የሆኑ ወጣቶች ብቻ ተጠቃሚ በሚሆኑበት በብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ፕሮጀክት ለወጣቶች የህይወት ክህሎት ስልጠና ፣ የዲጂታል ኮምፒውተር ክህሎት ስልጠናን ጨምሮ የስራ ላይ ልምምድ ስልጠና በመስጠት የስራ እድልን የማስፋት ስራ እየተሰራ ይገኛል።