የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ በከተሞች ተቋማዊ መሰረተ ልማት ማስፋፍያ /በUIIDP/ እና የ2014 ዓ/ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጸጸም ግምገማ አደረገ።

በመድረኩ የከተማ፣የክ/ከተማ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የ2014 ዓ/ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም የተሻለ መሆኑም ተጠቁሟል።

በመድረኩ የተገኙት የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ምክትልና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ አሸናፊ ኤልያስ ተግባራትን በቁርጠኝነት፣ በተቀናጀና በጀቱን ለታለመለት ዓላማ በማዋል በከተማዋ ከዚህ የተሻለ የልማት ስራዎችን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ የከተማዋን ተቋማዊ አሰራር የሚደግፍና የሚያጠናክር የሆነው የUIIDP ኘሮጀክት በተገቢው ሊፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከንቲባው አክለውም እንደ ሐዋሳ ከተማ በዚህ ዓመት ብቻ ከ390 ሚሊየን ብር በላይ የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆኑን የገለጹት ከንቲባው በቀጣይም በተጠናከረ የህብረተሰብ ተሳትፎ ከተማዋን የተሻለች ለነዋሪውም ሆነ ለሌላው ምቹ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ሚልክያስ ብትሬ ኘሮግራሙ በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋማት የጋራ ግንዛቤ ይዘው የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህ ኘሮጀክት ለከተማዋ መሰረተ ልማትና እድገት ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ በሩብ ዓመቱ ከዝግጅት ያለፈ አፈጻጸምም መተግበሩንም አክለዋል።

በመድረኩ በቀረበ ጽሁፍ በበጀት ዓመቱ አዲስ ከተያዙ 111 ኘሮጀክቶች መካከል በሩብ ዓመቱ 55 ያህሉን ወደ ተግባር ለማስገባት የጨረታ ሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

በመምሪያው ለመሰብሰብ ከታቀደው 433 ሚሊየን ብር ውስጥ በሩብ ዓመቱ 103 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ አፈጻጸሙም 25% ላይ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት የቅንጅታዊ አሰራርና የየተቋማቱ ሚና ውስንነት፣ እንዲሁም የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግና ሌሎችም በጥያቄና አስተያየት ካቀረቡት ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ለቀረቡ ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ጉድለቶችን በማረም የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖርም የተቀናጀ አሰራር እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ታህሳስ 2/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post