ለተከታታይ 10 ቀናት የሚቆይ የወተት ላሞችን በሆርሞን የማድራት (ሲንክሮናይዜሽን) ስራ በይፋ መጀመሩን የሐዋሳ ከተማ ግብርና ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የ2014 ዓም የወተት ላሞችን በሆርሞን የማድራት (ሲንክሮናይዜሽን) ስራ በዛሬው እለት በይፋ መጀመሩን የገለፁት አቶ አበባየሁ ላሊማ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊ የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
አቶ አበባየሁ አያይዘውም በዛሬው ዕለት የተጀመረው እንስሳትን በሆርሞን የማድራት (ሲንክሮናይዜሽን) ስራ በ12 የገጠር ቅበሌያት እንዲሁም በተመረጡ የከተማ አካባቢዎች በ13 የእንስሳት ህክምና ጣቢያዎች ለተከታታይ 10 ቀናት እንደሚሰጥም ገልፀዋል።
በሐዋሳ ከተማ ደረጃ 136 ሺህ የሚጠጉ የዳልጋ ከብቶች መኖራቸውን የገለፁት አቶ ገነነ ገላሳ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የእንስሳት እና አሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ ከእነዚህም ውስጥ 38 ሺህ የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ በ3 አይነት ዘዴ የማሻሻል ስራ መሰራቱንም ጨምረው ገልፀዋል።
በ3ቱ ዝርያ ማሻሻያ ዘዴዎች በያዝነው ዓመት ብቻ 13976 የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ ለማሻሻል ዕቅድ መያዙን የገለፁት አቶ ገነነ ገላሳ ዛሬ በተጀመረው በሆርሞን የማድራት (ሲንክሮናይዜሽን) የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ዘዴ 1500 የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ የማሻሻል ስራ መጀመሩን ገልፀው ከእነዚህም ውስጥ 900 የዳልጋ ከብቶች በሐዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ዝርያቸው የሚሻሻል መሆኑንም አመልክተዋል።
በሐዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በገራ ሪቀታ የእንስሳት ህክምና ጣቢያ በዕለቱ የወተት ላሞችን ዝርያ ለማሻሻል መጥተው የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው አርብቶ አደር ነዋሪዎች የእንስሳቶቻቸውን ዝርያ በማሻሻል ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን የተሻለ የወተት ምርት እና ለእርድ የሚሆን ከብት እያገኝን እንገኛለንም ብለዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
መስከረም/19/2014ዓም
ሐዋሳ