''ሰላም ይስፈን ጥቃት ይቁም'' በሚል መሪ ቃል የዓለም አቀፍ የነጭ ሪቫን ቀን በሐዋሳ ተከበረ።

በዓለም ለ30ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገር ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በተከበረው የነጭ ሪቫን ቀን በዓል ላይ ከሴክተር መ/ቤት፣ ከክ/ከተማ፣ ከፖሊስ፣ አቃቤ ህግ ባለሙያ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሣታፊ ሆነዋል።

የሐዋሣ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ወ/ጻዲቅ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድርሻ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በተለይም የነጭ ሪቫን ቀን ሲከበር ወንዶች ነጭ ሪቫን በደረታቸው ላይ በማድረግ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መቃወማቸውን የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ሀላፊዋ ተናግረዋል።

በዓሉን እንደ ቀን ከማክበር በላይ ማንም በተሰማራበት የሙያ መስክ ለፆታ እኩልነት ዘብ በመቆም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማንኛውንም አይነት ጥቃት በመቃወም ጭምር እንዲሆንም ነው ሀላፊዋ ያስረዱት።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች መምሪያ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኮሪያ በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማንኛውም አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ጉዳቶች ሊያስከትሉ የሚችሉ ጎጂ ድርጊቶችና ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም መንግስት ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን መሆኑን የገለፁት ምክትል ሀላፊዋ ህብረተሰቡ በግንባር ቀደምትነት ይህን ተግባር በባለቤትነት በመቀበል ከዳር ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው አያይዘው ሀላፊዋ ተናግረዋል።

በበዓሉ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር አቃቤ ሕግ መምሪያ አቶ አብርሐም አስታረቀኝ በመምሪያው ከፍተኛ አቃቤ ሕግ በሴቶችና ህጻነት ላይ የሚደረሱ ጥቃቶችን አስመልክቶ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በበዓሉ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመቃወም ሁሉም አጋርነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በዝግጅቱ ተሳታፊ የነበሩ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ተባባሪ ላለመሆን ቃል በመግባት ደረታቸው ላይ ነጭ ሪቫን አድርገዋል።

ለፕሮግራሙ መሳካት ድጋፍ ለደረጉ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 29/2014 ዓ.ም

ሐዋሳ

Share this Post