ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳርና ሩዝ ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑ ተገለፀ።

እነዚህ ምርቶች ጨምሮ ፓስታ ማካሮኒና እንቁላል ከውጭ ሲገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ ግብይት ሲፈፀም ከማንኛውም ቀረጥና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ላልተወሰነ ግዜ ነፃ እንዲሆኑ ተወስኗል።

የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ በማሰብ መንግሥት ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሩዝ ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ እና ታክስ ማሻሻያ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እና የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ለማሳደግ የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ዶ/ር ኢዮብ አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት የገንዘብ ሚኒስቴር ከፊስካል ፖሊሲ አኳያ የመሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን የጉምሩክ ቀረጥ እና ታክስ ማሻሻያ በማዘጋጀት ከነሐሴ 28 /2013 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በሚከተሉት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ እና ታክስ ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑን አመልክተዋል።

1. ስንዴ - ከውጭ ሲገባ ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

2. የምግብ ዘይት - ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

3. ስኳር - ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

4. ሩዝ - ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆን፣

5. ፓስታ እና ማካሮኒ - ከውጭ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምበት ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ እንዲሆን፣ እንዲሁም

6. የዶሮ እንቁላል - ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆን ተወስኗል።

ሚኒስትር ዴኤታው ማሻሻው ተግባራዊ ሲደረግ መንግሥት በብዙ ቢሊዮን የሚገመት ገቢ እንደሚያጣ በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።

የዋጋ ንረት በታክስ ብቻ የሚፈለገውን የዋጋ መቀነስ ስለማያመጣ አቅርቦትን ለመጨመር መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው ከነዚህ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ለስድስት ወር ተፈቅዶ የነበረው ያለውጭ ምንዛሬ ሸቀጦችን የማስገባት አሠራር ለሌላ ተጨማሪ ስድስት ወራት እንዲራዘም መደረጉንም ጨምረው ገልጸል፡፡

የንግድ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን የንግድ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም መንግስት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣተርና ገበያውን ለማረጋጋት ተጨማሪ የገንዘብ ፖሊሲን ጨምሮ ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንደሚወስድም ዶ/ር ኢዮብ ገልጸዋል፡፡

ዘገባው :- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖርት ነው።

Share this Post