በሐዋሳ ከተማ ለጀግናው የሀገር መከለከያ ሠራዊት የደም ልገሳ መርሀ ግብር ተደረገ

በተደረገው ከተማ አቀፍ የደም ልገሳ መርሀ ግብር ላይ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪ ተሳትፎ አድርገዋል።

"ደሜን ለግሳለሁ!!" በሚል መሪ ቃል የተደረገው ከተማ አቀፍ የደም ልገሳ መርሀ ግብርምን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ነው ያዘጋጀው።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በደም ልገሳው ላይ እንደተናገሩት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ሀገርን በምንችለው ሁሉ የማስጠበቅ ኃላፊነት የሁላችን ነው ብለዋል።

ከሀገር የሚበልጥ ምንም ነገር የለም ያሉት ከንቲባው በሐዋሳ ከተማ አመራሩ፣ ነጋዴው፣ ነዋሪው፣ ወጣቶች ደም ከመለገስ ባለፈ በገንዘብና በተለያየ መልኩ የሀብት ማሰባሰብ ስራው እየተከናወነ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የሐዋሳ ከተማ ብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፋ አቶ ዘማች እርጥብ ደም በለገሱበት ወቅት እንደተናገሩት ለመከላከያ ሰራዊት ቀደም ሲል የተለያዩ ድጋፎች ሲያደረግ ቆይቷል ብለዋል።

ይህ የአብሮነት ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያስታወሱት ሀላፊው ለዚህም እንደ ከተማ እየተደረገ ያለው የደም ልገሳ የህዝቡን አንድነት ከማሳየቱም በላይ ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀን እንደሆነ የሚጠቁም ነው ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ወጣቶች ሊግ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ለገሰ በበኩላቸው በአንድ ቀን ከህብረተሰቡ 2000 በላይ ደም ለመሰብሰብ በማቀድ መርሀ ግብሩ መዘጋጀቱን አስረድቷል።

ይህ የከተማዋ ወጣት ሚና ከደም ልገሳ በተጨማሪ ግባር ድረስ በመሄድ ሀገርን ለመጠበቅ ዝግጁ ስለመሆናቸውም ነው የሊጉ ሀላፊ ወጣት ታረቀኝ የተናገረው።

በደም ልገሳ መርሀግብሩ የተሳተፉ የከተማዋ ወጣቶች በበኩላቸው ሀገር በምትፈልገው ግዳጅ ሁሉ በመሰማራት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 9/ 2014 ዓ.ም

ሐዋሳ

Share this Post