በሐዋሳ ከተማ በ2ኛ ውሃ አቅርቦትና ሳንቴሽን ኘሮጀክት የተገነቡ የህዝብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ተመረቁ።

የፌደራል ውሃ ልማት ኮሚሽን ከአለም ባንክ በመተባበር የተሰሩ እነዚህ መጸዳጃና መታጠቢያ ቤቶች የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ እና የፌደራል ውሃ ኮሚሽን ባለስልጣን በተገኙበት ነው የተመረቀው።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ጸጋዬ ቱኬ ዛሬ የተመረቁ ኘሮጀክቶች በቀጣይ ለምንሰራው ከተማዋን ለሚመጥን የሳንቴሽን አገልግሎት ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ በውበቷ የምትታወቅ ብትሆንም በውስጧ ያሉ ያልለሙ አካባቢዎቸችን ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ የሚያለማው እንደሚሆን ነው ከንቲባው የተናገሩት።

ከከተማዋ እድገትና ከህዝቡ ፍላጎት አንጻር ይህንን መሰልና ሌሎች የልማት ስራዎችን ተደራሽ ማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቅ በመሆኑ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል።

የፌዴራል ውሃ ልማት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ወ/ሮ ሸዋነሽ ደመቀ ዛሬ የተመረቁት የህዝብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የከተማዋን ንጽህና ከመጠበቅ አንጻርም የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

ወ/ሮ ሸዋነሽ አክለውም በቀጣይ በጀት ዓመት ተጨማሪ 20 የጋራና የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የከተማዋን የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ለማዘመን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሐዋሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሀላፊ አቶ ዳዊት ሌላሞ በሀዋሳ ዛሬ የተመረቁ ኘሮጀክቶች ከ32 መጸዳጃ ቤቶች በኘሮጀክቱ በአጭር ጊዜ እንዲተገበሩ ከተቀመጡት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህም 22 የህዝብ እና 10 የጋራ መጸዳጃ ቤቶች መሆናቸውን ነው አቶ ዳዊት ያከሉት።

ከከተማዋ ህዝብ የመጸዳጃ ቤት ፍላጎት አንጻር በጣም ጥቂት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳዊት የቦታ ዝግጅትና ሌሎች ሁኔታዎች ሲሟሉ ተጨማሪ መጸዳጃ ቤቶች እንደሚገነቡም አረጋግጠዋል።

የዚህ ኘሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ እንደገለጹት የነዚህ መጸዳጃና መታጠብያ ቤቶች መገንባት የግልና የአካባቢያችንን ንጽህና ከመጠበቅ በላይ በጽዳቷ የምትታወቀውን ሀዋሳ ንጽህና የምናረጋግጥበት ይሆናል ብለዋል።

ተጠቃሚዎቹ አክለውም ኘሮጀክቱ ከዚህ ቀደም የሚከሰትብንን የጤና ችግር የሚቀርፍልን ይሆናልም ብለዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ነሐሴ 19/ 2013 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post