በሐዋሳ ከተማ በ2014 ዓ/ም በጀት ዓመት በልዩ ትኩረት በሚጀመር ኘሮጀክት ዙሪያ ውይይት ተደረገ።

በታቦር ተራራ እና በሐዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ዙሪያና በታቦር ተራራ በ2014 ዓ/ም ለማስጀመር በታቀደ ኘሮጀክት ጥናት ዙሪያ የተደረገው ውይይት ከከተማዋ አመራር አካላት ጋር ነው።

ይህ የ7.25 km ኘሮጀክት በስድስት ደረጃ ተከፋፍሎ በተለዩ ቦታዎች የሚተገበር ሲሆን በአረንጓዴ ልማት ያሸበረቁና ልዩ ልዩ ዘመናዊ የመዝናኛ ቦታዎች የተካተቱበት ነው።

በታቦር ተራራ እና በሐዋሳ ሀይቅ ዙሪያ የሚተገበረው ይህ ልዩ ኘሮጀክት ለከተማዋ ታላቅ እና እንደ ልዩ ምልክት የሚታይ ኘሮጀክት ነው ያሉት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ናቸው ።

ከንቲባው ይህ ኘሮጀክት የከተማዋን አረንጓዴ ውበት፣ እድገት፣ የቱሪስት ፍሰት ከፍ ከማድረጉ ባሻገር ገቢን ከማሳደግና የከተማዋን ተመራጭነት ከማጉላት አንጻር እንደ ሀገርም የጎላ ሚና ያለው ከመሆኑም ባለፈ ከምስራቅ አፍሪካ ካሉ ከተሞች በቱሪዝምና በኢንቬስትመንት የተመራጭ እንድትሆን የሚያስችል ነዉ ብለዋል ።

ኘሮጀክቱ የህዝብ ነው፣ ከተባበርንም ማሳካት እንችላለን ያሉት ረ/ኘሮፌሰር ጸጋዬ በቀጣይም ከከተማዋ ህዝብ፣ ከባለሀብቶች፣ ከምሁራን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሁሉ ውይይት የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

ስለ ኘሮጀክቱ ገለጻ ያቀረቡት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሀላፊ አቶ ወርቁ ቶማስ ናቸው።

አቶ ወርቁ እንደ ሐዋሳ ከተማ ሊተገበር የታቀደውን ይህ ኘሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚፈጸም ሲሆን በመድረኩ የተነሱ ተጨማሪ ሀሳቦችም የዲዛይኑ አካል እነደሚሆኑ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ አመራሮች በበኩላቸው ኘሮጀክቱን አስመልክቶ በቀረበው ምስል እጅግ መደሰታቸውን ሲገልጹ ለሚመለከታቸው አካላት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ ኘሮጀክት ለከተማው የሚኖረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ ለኘሮጀክቱ መሳካት የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።

ኘሮጀክቱ እንዲፋጠንም ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም በልዩ ትኩረት እንዲመራም ነው ሀሳብ ያቀረቡት።

የሐ/ከ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ሐምሌ 26/ 2013 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post