በሐዋሳ ከተማ በ41 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ቡርቂቶ ሆቴል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በምርቃቱ ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ስራ የጀመረው ይህ ሆቴል የስራ ዕድል ከመፍጠርና የከተማውን የቱሪዝም አቅም ከማሳደግ ረገድ ወሳኝነት እንዳለው ገልፀዋል።

በከተማው ባለሀብት በአቶ ለገሰ ላሚሶ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በታቦር ክፍለ ከተማ በፋራ ቀበሌ በ41 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ይህ ባለ ሶስት ወለል የሆቴል ህንፃ 36 መኝታ ክፍሎች እና 11 የንግድ ሱቆች ያሉት ሲሆን የሆቴልና የካፍቴሪያ አገልግሎት እንደሚሰጥም የሆቴሉ ባለቤት አቶ ለገሰ ላሚሶ ገልፀዋል።

በያዝነው በጀት ዓመት እንደ ከተማ በርካታ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ተቀብለናል ያሉት ክቡር ከንቲባው የኢንቨስትመንት ህግን በመከተል ለከተማው ተጨማሪ እድገት ለሚያመጡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንሰጣለንም ብለዋል።

በአንድ አመት ከአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በ41 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ስራ የጀመረው የሐዋሳ ቡርቂቶ ሆቴል ለ63 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በግንባታው ወቅት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የሆቴሉ ባለቤት አቶ ለገሰ ገልፀዋል።

ሆቴሉ የተገነባበት ቦታ በጨረታ በተገዛ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ መሆኑን የገለፁት ባለሀብቱ ለዚህም በዓመት ከ101 ሺህ ብር በላይ የሊዝ ክፍያ እንደሚከፍሉ በመጠቆም ከዚህ የተሻለ ስራ በመስራት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር አቅም ቢኖረንም ለኢንቨስትመንት የሚሆን ከቦታ እጥረት አንፃር በሚፈለገው ልክ መሄድ አልቻልንም ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራ የምንሰራበት ቦታ ቢያቀርብልን ደረጃውን የጠበቀ ስራ በአጠረ ጊዜ ውስጥ በመስራት ለብዙዎች የስራ እድል ለመፍጠር እና ለከተማው የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አስተዋፅኦ ለማበርከት በሙሉ አቅማችን በመንቀሳቀስ የበኩላችንን እንወጣለንም ብለዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

11/3/2014ዓም

ሐዋሳ

Share this Post