ተገደን የገባንበት የህልውና ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት በአጠረ ግዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረጋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ድጋፍ በማድረግና በማሰባሰብ ላይ የሚገኙ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የመሀል ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ገለፀዋል።
ክፍለ ከተማው ለህልውና ዘመቻው የሚያደርገውን ህብረተሰብ አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የክፍለ ከተማው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤ መሳይ ገልፀዋል።
አቶ ትንሳኤ አያይዘውም ክፍለ ከተማው በክልል እና በከተማ ደረጃ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ የህልውና ዘመቻውን በድል ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ስራዎችን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዚህም ህብረተሰብ አቀፍ የድጋፍ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል እስካሁን በክፍለ ከተማ ደረጃ በገንዘብ ከ1.53 ሚልዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን አቶ ትንሳኤ መሳይ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አራት የዕርድ ከብት፣ ዘጠኝ በግና ፍየል እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ምግብ ነክ ቁሳቁሶች እና የተለያዩ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማሰባሰብ መቻሉን እና ድጋፍ ማሰባሰብ ስራው እስከመጨረሻው ሰዓት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያ ሀገራችንን የማዳን ስራ እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ደሞዜ አርገቶ የመሀል ከተማ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ እንደ ክፍለ ከተማ በግንባር በመዝመት፣ ተጨባጭ ድጋፎችን በማድረግ እና አካባቢን በንቃት የመጠበቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
የክፍለ ከተማው ወጣቶች፣ ሴቶች አጠቃላይ ነዋሪው በተለያየ መንገድ ለሀገራዊ ጥሪው በከፍተኛ ተነሳሽነት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ደሞዜ ከዚህ ጎን ለጎን የልማት ስራዎችን የማፋጠን ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የክፍለ ከተማው ሴቶች ሊግ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ስንቅ የማዘጋጀት ስራ እየሰራን እንገኛለን ያሉት የክፍለ ከተማው ሴቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ላሌ በበኩላቸው የገብስ፣ ጤፍና የበቆሎ ዱቄት፣ ፓስታ መኮሮኒ፣ ሳሙናና የተለያዩ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ህዳር/15/2014 ዓ/ም
ሐዋሳ