በሐዋሳ ከተማ የሐይቅ ዳር ክ/ከተማ አስተዳደር ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ልጆች የዩኒፎርም ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ የተደረገው በገበያ ዳርና ጉዱማሌ ቀበሌ ለሚገኙ 100 ተማሪዎች ሲሆን 85ሺህ ብርም ወጪ ሆኖበታል።

የክ/ከተማው ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ አበራ ደገፉ ድጋፉን ላሰባሰቡ ለክ/ከተማው ባለሙያዎች እና በድጋፉ ለተባበሩ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ አበራ ሀገራችን አሁን በውስጥና በውጭ ባንዳዎች እንድትመሰቃቀል እየተደረገ ባለበት ወቅት ለህጻናት የሚያስፈልጋቸው ይሄ ሳይሆን የትምህርት ቁሳቁስ ነው በማለት የተሰራው ስራ እጅግ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የዛሬ ድጋፍ ተቀባይ ህጻናትም ተምራችሁና ተለውጣችሁ እናንተም ነገ ለሌላው ወገናችሁ የምትደግፉ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

ከማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረት ጋር በመተባበር በተለያየ ጊዜ ጊዜውንና ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የክ/ከተማው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዶክተር ዶርሲሶ ናቸው።

አቶ ዶክተር ድጋፉ ከተለያዩ ግለሰቦች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ መሆኑን ገልጸው በክ/ከተማው ተመሳሳይ ድጋፍ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም ችግሩ የጎላበትን በመለየት አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለእነዚህ የነገ ሀገር ተረካቢ ታዳጊዎች የሚመለከተው አካል ልዩ ትኩረት በመስጠት ቀጣይነት ያለውን ድጋፍ እንዲያደረግም ነው አቶ ዶክተር ጥሪ ያቀረቡት።

ድጋፍ የተደረገላቸው ህጻናት በበኩላቸው ይህንን ዩኒፎርም ሊያሟሉ የሚችሉበት አቅም እንደሌላቸው ገልጸው በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 11/ 2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post