በሐዋሳ ከተማ የመናኸሪያ ክ/ከተማ ጉዌ ስታዲየም ቀበሌ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀን ሆነው እንደሚቆሙ ገለጹ።

ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ለ3ኛ ዙር የስንቅና ሌሎች ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑም ገለጸዋል።

ዛሬ በጉዌ ስታዲየም ቀበሌ በሾሪና ቂልጦ መንደር ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደርስ የስንቅ ዝግጅት ሲያደርጉ በሀገር መደፈር ቁጭት እስከ ግንባር ለመሄድ ዝግጁ መሆናቸውን በማስረዳት ነው።

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ፍጹም ግርማ እና ሌሎች ነዋሪዎች ለስንቅ ዝግጅቱ ከየቤቱ እህል የማሰባሰብ ስራ መስራታቸውን ገልጸው ከመንደሩ በጥሬ ገንዘብ ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማድረጋቸውን አክለዋል።

እስከመጨረሻውም የሚያደርጉት ድጋፍ እንደሚቀጥል ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ሀላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ወ/ጻዲቅ ሴቶች እያደረጉ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የሴቶች እንቅስቃሴና ቁጭት ድንበር ካለው የማይተናነስ ነው ያሉት ወ/ሮ ፍሬህይወት የስንቅ ዝግጅቱ በተለያየ አይነት የሚገለጽ ሲሆን የአልባሳትና የጥሬ ገንዘብንም ያካተተ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም ከ2.8 ሚሊየን በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ የአልባሳትና የስንቅ ዝግጅት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማድረስ እንደተቻለ ወ/ሮ ፍሬህወት ገልጸዋል።

ሽንፈትን በታሪኳ አስተናግዳ የማታቀው ሀገራችን አሁንም ድል እንደምትጎናጸፍ አምናለሁ ብለዋል ወ/ሮ ፍሬህይወት።

የሐ/ከ/አ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 13/ 2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post