በሐዋሳ ከተማ የአፈፃፀም ጉድለቶችን ለማረምና ጠንካራ አፈፃፀሞችን ለማስቀጠል ያለመ የህዝብ አስተያየት መቀበያ መድረክ ተካሄደ።

የሐዋሳ ከተማ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን እና ከተማ ልማት መምሪያ እንዲሁም በሐዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አፈፃፀም ዙሪያ የህዝብ አስተያየት መቀበያ መድረክ በዛሬው እለት አካሂዷል።

በመድረኩ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን እና ከተማ ልማት መምሪያ እንዲሁም የአስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የአምስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ከ8ቱም ክፍለከተማ ህብረተሰቡን ወክለው በተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ ውይይትም ተካሂዷል።

እንደ ከተማ በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በመጠንም ሆነ በጥራት መሻሻል እያሳዩ እንደሚገኝ የገለፁት የመድረኩ ተሳታፊ የህብረተሰብ ክፍሎች በጉድለት የታዩና መሻሻል ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮችም አንስተው ተወያይተዋል።

አቶ ደምሴ ዳንጊሶ የሐዋሳ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የህዝብ አስተያየት መቀበያ መድረኩ ህብረተሰቡንና አስፈፃሚውን አካል በማቀራረብ በከተማ ደረጃ የሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ጥራት ከማሳደግና የህዝብ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል።

የከተማ አስተዳደሩን የኮንስትራክሽንና የከተማ ልማት መምሪያ የ5ወራት አፈፃፀም ያቀረቡት አቶ ሚልክያስ ብትሬ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽን እና ከተማ ልማት መምሪያ ኃላፊ ባለፉት አምስት ወራት በህብረተሰብ ተሳትፎ በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የመድረኩ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጠቁዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀይሉ የተራ በበኩላቸው መምሪያው በሚያተኩርባቸው የንግድና የገበያ ልማት ዘርፍ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የገለፁ ሲሆን የህዝብ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቁ ቀሪ ስራዎችን ተቀራርቦ በመስራት ውጤት ማምጣት ይገባልም ብለዋል።

ምክር ቤቱ በሁሉም ዘርፎች ተገልጋዩን ህብረተሰብና አስፈፃሚውን አካል በማቀራረብ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ደምሴ ዳንጊሶ የዛሬውን መድረክ ላዘጋጀው የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምስጋና አቅርበዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ታህሳስ/7/2014ዓም

ሐዋሳ

Share this Post