ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2014 በጀት ዓመት በሶስት ወራት 1 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ።
የሐዋሳ ከተማን እድገት ለማስቀጠልም ሆነ የማህበረሰቡን በርካታ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ገቢን በተገቢው መሰብሰብ የግድ እንደሆነ የተናገሩት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ናቸው።
የገቢ ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ አንጻር ገቢን ለመሰብሰብ ሰፊ እድሎች መኖሩን ጠቁመው የገቢ አማራጮችን በተገቢው በመጠቀምና ህግን በማስከበር ጭምር እቅዱን ማሳካት ይገባል ብለዋል።
ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚቻለው በገቢ መሆኑን ያስረዱት ረ/ኘሮፌሰር ጸጋዬ ከዚህ በኋላ በየትኛውም ሁኔታ በከተማዋ ደረሰኝ የማይሰጥ፣ የማይቀበል እና ግብርን በወቅቱ የማይከፍል ማህበረሰብ ሊኖር አይገባምም ነው ያሉት።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅርጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ታምሩ ተፈሪ ይህንን እቅድ ለማሳካት የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ገቢን በተለመደው መንገድ ሳይሆን በንቅናቄ መተግበር ይጠበቃል ብለዋል።
አቶ ታምሩ አክለውም ደረሰኝ መስጠት ሲገባው ያልሰጠ ግብር ከፋይ አንድ ጤና ጣቢያ፣ አንድ ት/ቤት፣ መሠረተ ልማት.. ወዘተ እንዳፈረሰ ሊረዳ ይገባል ብለዋል።
ገቢ ማለት ሁሉም ነገር መሆኑን የገለጹት አቶ ታምሩ ለከተማዋ በዚህ ዓመት ምንም አይነት የድጎማ በጀት አለመኖሩን ገልጸው በዕቅድ የተያዙ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ ትላልቅ ኘሮጀክቶችም ሊሳኩ የሚችሉት ከከተማዋ ከሚሰበሰብ ገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
ድብብቆሽ የሚጫወቱ አንዳንድ ግብር ከፋይ ግለሰቦችን የልማት ጠያቂ የሆነው ማህበረሰብ ሊያወግዝ ይገባልም ብለዋል አቶ ታምሩ።
የመድረኩ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ለገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ተግዳሮት ያሏቸውን ሀሳቦች ለመድረኩ አቅርበው ምላሽም ተሰጥቷል።
ተሳታፊዎቹ አክለውም በ3ወር ውስጥ የታቀደውን የ1ቢሊየን ብር ገቢ እቅድ ለማሳካት ጠንክረው እንደሚሰሩ በመድረኩ ቃል ገብተዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
መስከረም 6/2014 ዓ/ም
ሐዋሳ