በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የህብረተሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ሐዋሳ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን እና የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ የንቅናቄ መድረክ ወቅት ነው።

አቶ ካሱ አሩሳ የሐዋሳ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተካሄደው በንቅናቄ መድረኩ ባደረጉት ንግግር በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የህብረተሰብ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነነትን የበለጠ ለማረጋገጥ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልፀዋል።

እንደ ሀገር የምንከተለውን መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፓሊሲ ስኬታማነት ለማረጋገጥ እንደ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች የሚሰጡት አገልግሎት ወሳኝነት እንዳለው የገለፁት አቶ ካሱ አሩሳ ዘርፉን በአግባቡ መምራት ቅድሚያ የሚሰጠው ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትም ሆነ በጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ትግበራ ከሚታዩ ችግሮች ፈጥኖ መውጣት ይገባል ያሉት አቶ ካሱ አሩሳ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንዲሁም ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጭምረው ገልፀዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙንጠሻ ብርሀኑ በበኩላቸው መድረኩ በአጠቃላይ እንደ ከተማ የጤና መድህን አገልግሎትን በሙሉ አቅም በማስተግበር ዜጎች በገንዘባቸው ልክ ሳይሆን በህመማቸው ልክ መታከም እንዲችሉ አመራሩን፣ ባለሞያውን እና ማህበረሰቡን ለማሳተፍ ያለመ የንቅናቄ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን አመራሩን በማቀናጀት፣ ህብረተሰቡን በማሳተፍና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎችን በማንቀሳቀስ፣ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በመተግበር የንፅህናና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ማሳለጥ የንቅናቄ መድረኩ ዋና ዓላማ መሆኑንም አቶ ሙንጠሻ ብርሀኑ ግልፀዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የ2013 ዓም የከተማው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ አፈፃፀም ግምገማ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተካሂዷል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/29/2014ዓም

ሐዋሳ

Share this Post