በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጀግናው ሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ተሸኙ።

ለወጣቶቹ በተደረገው አሸኛኘት የሲዳማ ክልል ር/መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞና ከፍተኛ አመራሮች፣ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እና የተለያዩ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ወጣቶቹ የሐገር ሉዓላዊነትንና የህዝብን ክብር ለማስጠበቅ በፍቃደኝነት የተነሳሱ መሆናቸውም ተገልጿል።

በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ር/መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጀግናው የሲዳማ ክልል ወጣቶች በፍቃደኝነት ወደ ሰራዊቱ ለመቀላቀል በመትመማቸው እጅግ ኮርተንባችኋል ብለዋል።

ር/መስተዳድሩ የትግራይ ህዝብ ውስን በሆኑ የጁንታ ቡድን ሽንገላ ሳይታለል የኢትዮጵያ ህዝብን በትግል እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል።

የሲዳማ አባቶች ጀግንነትን እንጂ ፍርሀትን አላወረሱንም ያሉት ር/ መስተዳድሩ እነዚህ ጀግና የሲዳማ ወጣቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ይህ ጸረ ሰላም ቡድን እስኪወገድና የሀገር አንድነት እስኪጠበቅ ድረስም የሲዳማ ህዝብ በገንዘብ፣ በአይነት፣ በስንቅ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ነው ር/ መስተዳድሩ የተናገሩት።

ወጣቶቹ ከሲዳማ አባቶች እጅ የፌዴራል እና የሲዳማ ክልል ሰንደቅ ዓላማ የተቀበሉ ሲሆን ድል ከነሱጋር እንዲሆንም በሲዳማ አባቶች ተመርቀው ተሸኝተዋል።

Share this Post