በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሐዋሳ ከተማ በመከበር ላይ ባለው 34ኛው የዓለም የቱሪዝም ቀን በመሳተፍ ላይ ላሉ ባለድርሻ አካላት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በታቦር ተራራ አናት ላይ የእራት ግብዣ መርሀ ግብር አካሄደ።

ከሐዋሳ ከተማ የቱሪዝም መስህቦች አንዱ በሆነው በታቦር ተራራ አናት ላይ በተካሄደው የእራት ግብዣ መርሀግብር በሲዳማ ብሓራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚከበረው የቱሪዝም ቀን በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር፣ አቶ በየነ በራሶ የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳደር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል እና የሐዋሳ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ማምሻውን ተካሂዷል።

በእራት ግብዣ መርሀ ግብሩ ባደረጉት ንግግር የቱሪዝም ዘርፍ እንደ ሀገር በአግባቡ ያልሰራንበትና ተገቢውን ጥቅም ያላገኘንበት ዘርፍ ነው ያሉት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ከፍ እንድትል እና የተሻለ እድገት እንድታስመዘግብ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን መደገፍና ማሳደግ ይገባልም ብለዋል።

ዘርፉን የሚያግዙ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎችን በማስፋፋትና በማጠናከር የቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባም ከንቲባው ጠቁመዋል።

ባሳለፍነው ዓመት ሐዋሳን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ስራ መሰራቱን የገለፁት ከንቲባው ዘንድሮም የክልሉ መንግስት ለቱሪዝም ዝርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የክልሉንና የከተማውን የቱሪዝም መስህብነት የሚያሳድጉ ስራዎችን ለመስራትና የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

መስከረም/14/2013ዓም

ሐዋሳ

Share this Post