በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለሐገር ደጀን ለመሆን የተዘጋጁ 1 ሺህ ወጣቶች ተመረቁ።

ወጣቶቹ የአንድ ወር ስልጠና አጠናቀው ዛሬ በሐዋሳ ስታዲየም አርተፍሻል ሜዳ ነው የተመረቁት።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብረሃም ማርሻሎ አካባቢያችንን ብሎም ሀገርን መጠበቅ የሚያስችል ስልጠና ወስዳችሁ ለመንግስት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ በመሆናችሁ እንኮራባችኋለን ብለዋል።

አቶ አብርሃም ከተማችን ለነዋሪዎቿ እና ለእንቨስትመንት ያላትን ምቹነት ከማጎልበት ጎን ለጎን ለጁንታው ሀይል የማትመች እንድትሆን መስራት ከተመራቂዎች ይጠበቃል ብለዋል።

አንድነቷ ተጠብቆ የተረከብናትን ሀገራችን ለቀጣይ ትውልድ ስናስተላልፍ ሳትከፋፈል ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ አብርሃም ለጁንታውም ሆነ ለምእራባዊያን እኩይ አላማ ሳንበረከክ የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናረጋግጥ ይሆናል ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክት ከተማችንም ሆነ ሀገር ከኛ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችሁ የሚወደስ ተግባር ነው ብለዋል።

ከንቲባው ግንባር በመሄድም ሆነ የአካባቢያችሁን ሰላምና ጸጥታ በንቃት በመጠበቅ ይህንን ሀገር ጎጂ ተግባር በጋራ ማምከን ይጠበቃልም ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ጠላቶች እንደፈለጉ እንዲሆኑባት አንፈቅም ሲሉም ከንቲባው መልእክት አስተላልፈዋል።

ተመራቂ ወጣቶች በበኩላቸው ኢትዮጵያ የተገመደችበት ገመድ በወሬ የሚበጠስ አለመሆኑን ገልጸው የቀደመ ታሪኳን ዛሬ በዘመናችን እንደግመዋለን ብለዋል።

ተመራቂዎቹ አክለውም መንግስት ለሚያቀርበው ማንኛውም ጥሪ ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልጹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያ በመከተል ወደ ግንባር ለመሄድ ያላቸውን ዝግጁነት ተናግረዋል።

የሐ/ከ/አ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 16/ 2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post