በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት የበቃና የሰለጠነ ስራ ፈላጊ ዜጋ ለኢንዱስትሪው ለማቅረብ በትኩረት እየተስራ መሆኑ ተገለፀ።

በክፍለ ከተማ ደረጃ የስራ ፈላጊ ልየታ ተሰርቶ በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና በጨርቃጨርቅ ዘርፍ የአጭር ጊዜ ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸው ክህሎታቸውን ከማሳደጉ በተጨማሪ የስራ ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው በስልጠና ወቅት ያነጋገርናቸው ሰልጣኞች የገለፁ ሲሆን ከስልጠናው ብኋላ የስራ እድል እንዲመቻችላቸውም ጠይቀዋል።

እንደ ከተማ ከዚህ ቀደም በኮብል ስቶን ንጣፍ ስራ ተሰማርተው የነበሩ ማህበራትን ሙሉ በሙሉ የማሸጋገር ስራ መሰራቱን የከተማው ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ የገለፀ ሲሆን በዘንድሮው ስልጠና የወሰዱና ልየታ የተደረገላቸው ስራ ፈላጊዎች ብቻ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ሶስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማእከላት በክፍለ ከተማ ደረጃ ልየታ ለተደረገላቸው ስራ ፈላጊዎች የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን በመስጠት የበቃና የሰለጠነ ስራ ፈላጊ ዜጋ ለኢንዱስትሪው ለማቅረብ በትኩረት እየተስራ መሆኑም ተመላክቷል።

አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ እንደ ከተማ በያዝነው በጀት ዓመት 22900 የሚሆኑ ስራ ፈላጊ ዜጎችን ለመለየት በእቅድ መያዙን እና 22 ሺህ ስራ ፈላጊ ዜጎች በስምንቱም ክፍለ ከተማ መለየት መችሉንም ጠቁመዋል።

ከእነዚህም ውስጥ 3200 የሚሆኑት የድግሪ ምሩቃን ሲሆኑ 6000 የሚሆኑት ደግሞ በተለያየ የዲፕሎማ ደረጃ ምሩቃን መሆናቸውንም አቶ ታረቀኝ አክለው ገልፀዋል።

የልየታ ስራው ከተከናወነ ብኋላ በከተማ ውስጥ ያሉ የስራ አማራጮችን በመጠቀም በአረንጓዴ ልማት በጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ (በኮብል ስቶን)፣ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት፣ በግንባታ ስራ እና በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም በሌሎች ጥሪት ማፍሪያ ዘርፎች የስራ እድል የመፍጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ እስካሁን መንግስታዊ ድጋፍ በሚሹ ጉዳዪች ላይ የአጭር እና የረዥም ጊዜ ስልጠና በመስጠት፣ የብድር አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም የማምረቻና የመሸጫ ቦታ በማመቻቸት ለ8600 ስራ ፈላጊ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ጨምረው ገልፀዋል።

በከተማው በሚገኙት በ3ቱ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች በመደበኛና በአጭር ጊዜ የስልጠና ዘርፎች የሰለጠነ፣ የበቃና የተመዘነ የሰው ኃይል ለማቅረብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ገዛሀኝ ወ/ሰንበት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ልማት መምሪያ ኃላፊ በአሁኑ ጊዜ ከከተማው ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ጋር ቅንጅት በመፍጠር ለበርካታ ስራ ፈላጊ ዜጎች የአጭር ጊዜ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል።

በተቋማቱ በተለይ የገበያ ፍላጎት ባለባቸው ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ ገበያ ተኮር ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ገዛሀኝ ስራ ፈላጊ ዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

የሐዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን እና የሰው ኃይል ልማት ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መለሰ ዲዳሞ በበኩላቸው ከከተማ ማዕከል ተለይተው በተለያዩ ገበያ ተኮር የስልጠና ዘርፎች 6000 ተማሪዎችን ለማሰልጠን በእቅድ መያዙን ገልፀው እስካሁን ከ3000 በላይ ማሳካት መቻሉን እና በአሁን ሰዓት ከ700 በላይ ሰልጣኞች በስልጠና ላይ እንደሚገኙም በመጠቆም።

አቶ መልካሙ በራሳ የሐዋሳ ከተማ ተግባዕረ እድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ዲን ተቋሙ በ16 የሙያ ዘርፎች 1421 ነባር መደበኛ ሰልጣኞችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ መደበኛውን ሳይጨምር ለ6ሺህ ዜጎች የአጭር ጊዜ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን የገለፁት አቶ መልካሙ በራሳ 1023 ወጣቶች የአጭር ጊዜ ስልጠናቸውን አጠናቀው ለምዘና መድረሳቸውን እና ከእነዚህም ውስጥ 46ቱ አካል ጉዳተኞች መሆናቸውንም ገልፀዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/21/2014/ዓም

ሐዋሳ

Share this Post