በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣው አዲስ የንግድ ፍቃድ ፍላጎት ሐዋሳ ለንግድ እንቅስቃሴ ይበልጥ ተመራጭ ከተማ መሆኗን እንደሚያሳይ የሐዋሳ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀይሉ የተራ ገለፀዋል።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ለመምሪያውና ለስምንቱም ክፍለከተማ የንግድ ምዝገባና መረጃ አያያዝ፣ ለንግድ ዕድሳትና ፈቃድ ሰጪ ባለሞያዎች እና አመራር አካላት በንግድ ምዝገባና መረጃ አያያዝ እንዲሁም በንግድ ዕድሳትና ፍቃድ አሰጣጥ የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
በሐዋሳ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት የታየው የአዲስ ንግድ ፍቃድ ፍላጎት መጠነ መጨመር የሐዋሳ ከተማ ለንግድ ተመራጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እያደገ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን የገለፁት አቶ ሀይሉ የተራ በከተማው ያለውን አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ የመረጃ አያያዝ፣ የንግድ ፍቃድና እድሳት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና በማረጋገጥ የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ህጋዊ አሰራርን ብቻ በመከተል የተቀላጠፈ የንግድ አገልግሎት ለመስጠትና የከተማዋን ተመራጭነት የበለጠ ለማሳደግ በነባር እና በተሻሻሉ የንግድ አዋጆችና የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ የባለሞያውንና የአመራሩን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ሀይሉ ጨምረው ገልፀዋል።
በንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዙሪያ በወጡ አዋጆች የህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ስልጠናውን የሰጡት ወ/ሮ አብነት በለጠ በደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከቅድመ ፍቃድ ጀምሮ እስከ መረጃ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ከመቅረፍ ረገድ የስልጠናው ጠቀሜታ የጉላ መሆኑን ገልፀዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በከተማ ደረጃ እና በክፍለከተማ የሚገኙ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ እንዲሁም የመረጃ አያያዝ በለሞያዎችና አመራር አካላት ተሳታፊ መሆናቸው በሁሉም ደረጃ ወጥነት ያለውና ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ወ/ሮ አንድነት ጨምረው ገልፀዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ የከተማና የክፍለከተማ ባለሞያዎችና አመራር አካላት በበኩላቸው በነባርና አዲስ በተሻሻሉ የንግድ ህግ ማዕቀፎች ዙሪያ ልጠና መሰጠቱ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ተገልጋይ ተኮር አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ታህሳስ/26/2013/ዓም
ሐዋሳ