በከተማዋ ለሚገኙ የቅርጫት ኳስ ስፖርት የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አዘጋጅነት ነው በከተማዋ የአንደኛ ደረጃ ቅርጫት ኳስ ስፖርት የአስልጣኝነት ስልጠና የተሰጠው።

መምሪያው ለቅርጫት ኳስ ስፖርቱ እድገት የሚያግዝ ስልጠና ስለመስጠቱ የገለፁት የመምሪያው የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ሐሜሶ ናቸው።

በ2013 በጀት አመት እንደ ከተማ በቅርጫት ኳስ ስፖርት የተመዘገበው ውጤት አመርቂ ስለመሆኑም ነው ሀላፊው ያስረዱት።

ይህን እምርታም በላቀ መልኩ ለማስቀጠል ስፖርቱን በእውቀት የታገዘ እንዲሆን ስለማስፈለጉ የተናገሩት አቶ ጥላሁን ለዚህም የአንደኛ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

ስልጠናውን የወሰዱ አካላትም በፕሮጀክት ለሚሰለጥኑ ታዳጊዎች ደጋፍ እንደሚያደርጉ ሀላፊው አያይዘው ተናግረዋል።

የመምሪያው የስፖርት ዘርፍ ስልጠናና ውድድር ዳሬክቶሪት ዳይሬክተር ወ/ሮ ማዕዛ እንደገለጹት ሰልጣኞቹ ከ8ቱም ክ/ከተማ የተውጣጡ ሆነው ላለፉት 15 ቀናት ስልጠናውን መከታተላቸውን ተናግረዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው አቅማቸውን እንደገነቡ አስረድተው ይህም ለወጣቶች ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ተመሳሳይ ስልጠናዎች የቅርጫት ኳስ ስፖርቱን ለማጎልበት በመምሪያው እና በሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እንዲሰጡም ነው ሰልጣኞቹ አያይዘው የጠየቁት።

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይም የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ያዘጋጀውን የምስክር ወረቀት ሰልጣኞቹ ከአቶ ጥላሁን ሀሜሶ እጅ ተረክበዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 1/2014 ዓ.ም

ሐዋሳ

Share this Post