በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አካባቢዎች በተሰራው የመንገድ ከፈታ፣ ጥገናና የእድሳት ስራ የረዥም ጊዜ ጥያቄያችን ተመልሷል ሲሉ ተጠቃሚ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የኤልዲፒ ጥናትን እና የሐዋሳ ከተማ የ10 ዓመት መዋቅራዊ ፕላን ትግበራ አካል የሆኑ እንዲሁም ለነዋሪዎች የረዥም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ የመንገድ ከፈታ ስራዎች በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በዳቶና በሌሎች ቀበሌያት ማከናወን ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በህብረተሰብ ተሳትፎ ሐዋሳ ከተማን የማስዋብ ዕቅድ ተነድፎ እስካሁን 10 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ የተደረገበት የአረንጓዴ ልማት ስራ በህብረተሰብ ተሳትፎ ብቻ መከናወኑም ተጠቁማል።

በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች በተጨማሪም ቀደም ብለው በመንግስት ዕቅድ የተያዙና ለሐዋሳ ከተማ ውበት እሴት የሚጨምሩ አዳዲስና ነባር ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመጀመርና የተጀመሩትን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በጥብቅ የአመራር ዲሲፕሊን፣ በህብረተሰብ ተሳትፎና በከፍተኛ ወጪ ለዓመታት የተጠራቀሙ የረዥም ጊዜ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እያገኙ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከተማችን ሐዋሳ ውብ፣ ፅዱ አረንጓዴ እና ለኑሮ ተስማሚ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹና ተመራጭ ከሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል በቀዳሚነት ተጠቃሽ ከተማ መሆኗን የገለፁት ክቡር ከንቲባው የከተማዋን ውበት፣ ፅዳትና አረንጓዴነት አጠናክሮ በማስቀጠል ይበልጥ ተመራጭ ለማድረግ የከተማዋ ነዋሪ እና የአመራር አካላት ጥምረት፣ የማይቋረጥ ጥረት እና ርብርብ ወሳኝነት አለው ብለዋል።

አስተዳደሩ በሁሉም ዘርፍ የነዋሪውን ተሳትፎ በማረጋገጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀቶችን በማጠናከር፣ በመደገፍና ክትትል በማድረግ የልማት አጀንዳዎችን በመተግበርና በማስተግበር የመሰረተ ልማት ስራዎችን እንዲሁም የከተማ ፅዳት፣ ውበትና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በአዲስ መንገድና ስልት በማከናወን ሐዋሳን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በርካታ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በያዝነው የ2014 በጀት ዓመት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለከተማዋ ፈጣን ዕድገት ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የአካባቢ ልማትና የከተማ ማስዋብ ስራዎች ለማከናወን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም ክቡር ከንቲባው ገልፀዋል።

ይህን ስራ ከዳር ለማድረስ በከተማ ማዕከል ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ስራዎችን ከከተማ ወደ ክፍለ ከተማ፣ ቀበሌ፣ ብሎክና መንደር በማውረድና በተለይ ለህብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀቶች ትኩረት በመስጠት ተጨባጭ ስራዎችን በማከናወን ውጤት ማምጣት ተችሏል ያሉት ደግሞ አቶ ሚልክያስ ብትሬ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው።

የህብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የገለፁት አቶ ሚልክያስ አያይዘውም የነዋሪውን የልማት ጥያቄ ከከተማው እድገት ጋር አጣጥሞ በተሻለ ፍጥነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

አቶ ታሪኩ ታመነ በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት መምሪያ ም/ኃላፊና የማስፈፀም አቅም ግንባታና የአካባቢ ልማት ዘርፍ ኃላፊ በበኩላቸው ከከተማ ማስዋብና ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ከመስከረም ወር ወዲህ በህብረተሰብ ተሳትፎ ብቻ ከ30ሺህ ካ.ሜ በላይ የመንገድ ዳርቻዎች በተለያዩ አካባቢዎች ማልማት እንደተቻለ ገልፀዋል።

በያዝነው ዓመት እንደ ከተማ ትኩረት ከተሰጣቸው ስራዎች ውስጥ የመንገድ ከፈታ፣ ግንባታ እና ጥገና ስራ አንዱ መሆኑን የገለፁት አቶ ታሪኩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ሳይጨምር በዳቶ ቀበሌ አራት ወሳኝ መንገዶች ተለይተው ለባለ ይዞታዎች ተገቢውን ካሳ እና ምትክ ቦታ በመስጠት 4ሜትር እና ከዛ በታች የጎን ስፋት የነበራቸውን ከ20 ኪ.ሜ በላይ መንገዶች የጎን ስፋታቸውን ከ20 ሜትር በላይ በማሳደግ በመዋቅራዊ ፕላን መሰረት የመንገድ ከፈታ ስራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ በሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በጋራ ሪቀታ እና በሌሎች ቀበሌያት ከ18 ኪ.ሜ በላይ የመንገድ ከፈታ፣ ጥገና፣ ሬዳሽ እና ሴሌክት የማልበስ ስራ መከናወኑንም ኃላፊው ገልፀዋል።

የአስፓልት መንገድ ግንባታን በተመለከተ እንደ ከተማ ከ7 ኪ.ሜ በላይ መንገድ ለመገንባት በእቅድ የተያዘ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ከአስፓልት መንገዶች በተጨማሪ በ39 ሎት ከ19.9 ኪ.ሜ በላይ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ ለማከናወን በእቅድ መያዙንም እንዲሁ አቶ ታሪኩ ገልፀዋል።

የግንባታ ስራቸው ተጠናቆ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል የታቦር ኢኮ ቱሪዝም አንዱ አካል የሆነውና የዲዛይን ስራው ተጠናቆ የጨረታ አሸናፊው የተለየው የታቦር ተራራ መወጣጫ ደረጃ ግንባታ ስራ፣ የሐዋሳ ሐይቅ ዳርቻን የማስዋብ ስራ፣ በግንባታ ላይ ያለው የሻፌታ ታወር ግንባታ ስራ ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር ተዳምረው ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሚፈጥሩም ነው አቶ ታሪኩ ያመላከቱት።

በነባር እና በመልሶ ማልማት በተፈጠሩ አዳዲስ አካባቢዎች እንዲሁም ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች የመብራት እና የውሀ ጥያቄዎችን በከፍተኛ ወጪ ለመመለስ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አቶ ታሪኩ ገልፀዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/7/2014ዓም

ሐዋሳ

Share this Post