የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንዲሁም ሌሎች የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች የሊያና ሄልዝ ኬር ቅርንጫፍ የሆነውንና ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት በአዲስ መልክ የተደራጀውን የኮቪድ ማገገሚያና የካንሰር ህክምና ማዕከል በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርና የሊያና ሄልዝ ኬር የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሞያዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ለዓዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ ልዩ ዝግጅትም ተካሂዷል።
በልዩ ዝግጅት ፕሮግራሙና በጉብኝቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር 2013 ዓም እንደ ሐዋሳ ከተማ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት ስራዎች በልማትና በሰላም ትልቅ ስኬት የተመዘገብበት ዓም መሆኑን ገልጸዋል።
በመጪው 2014 ዓም በተለይ በጤናው ዘርፍ ሐዋሳ ከተማን በምስራቅ አፍሪካ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ትልቅ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መግባቱን ክቡር ከንቲባው ገልፀዋል።
ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ አያይዘውም በጤና አገልግሎት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።
እንደ ከተማ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና በዘርፉ ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ በጋራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ሐዋሳን በጤናው ዘርፍ ይበልጥ ተመራጭ እና የጤና ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርጉ አገልግሎቶችን በመስጠት በዘርፉ ከተሰማሩ የግል ተቋማት መካከል ሊያና ሄልዝ ኬር በቀዳሚነት የሚጠቀስ መሆኑንም ከንቲባው ጨምረው ገልፀዋል።
በመንግስት ዓቅም ብቻ የማህበረሰብን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ማሟላት አይቻልም ያሉት የሊያና ሄልዝ ኬር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ግርማ አባቢ በበኩላቸው መንግስትና የግሉ ዘርፍ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ በመግለፅ ተቋማቸው ከዚህ ረገድ ተጨባጭ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ነሐሴ/27/2013ዓም
ሐዋሳ