ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ ለፕሬዚዳንት ባይደን አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ በቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ዜጎችን ለከፋ ችግር መዳረጉን አስረዳ

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ በቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ዜጎችን ለከፋ ችግር መዳረጉን አብራርቶላቸዋል።

በጋምቤላ ክልል የተወለደውና በአሜሪካ ሚኔሶታ ኦስቲን የምክር ቤት አባል የሆነው ኦባላ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመሰረተ ልማት ጉዳዮች ላይ ባተኮረው ስብሰባ ንግግር አድርገው ሲወጡ በአካል አግኝቶ አነጋግሯቸዋል።

በዚህ ወቅትም ህወሓት በኢትዮጵያ በፈጠረው ግጭት ምክንያት ኢትዮጵያውያንን ለከፋ ችግርና ስቃይ መዳረጉን ገልጾላቸዋል።

ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር በነበረው ቆይታ በተወለደበት ጋምቤላ ከዚህ ቀደም በአሸባሪው ህወሃት ከተጠነሰሰ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተርፎ መውጣቱን እንደገለጸላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው መረጃ አስታውቋል።

ከዚህ ባለፈም ህወሓት መራሹ መንግስት ባለፉት 27 አመታት አኝዋኮችን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰባቸውን ሰቆቃ በተመለከተም ማስረዳቱን ይገልጻል።

በወቅቱም ፕሬዚዳንቱ የተሰማቸውን ሃዘን እንደገለጹለትም ነው በጽሁፉ ያሰፈረው።

በተጨማሪም በህወሓት የግጭት ሴራ እስካሁን ድረስ መላው ኢትዮጵያውያን እያሳለፉትና እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ በተመለከተ እና አሜሪካም ይህን ሽብርተኛ ቡድን መደገፍ እንደሌለባት ማብራራቱንም ጠቁሟል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ዘገባው የኤፍ ባ ሲ ነው።

Share this Post