ከአዲስ አበባ ቀጥሎ የመጀመሪያው የዲኤስቲቪ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ በሐዋሳ ከተማ ተከፈተ።

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የሲዳማ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና ት/ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሳ እና የክልሉ አመራሮች፣የሐዋሳ ከተማ ም/ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ሚልክያስ ብትሬ እና የከተማው አመራሮች ተገኝተዋል።

የሲዳማ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሳ ሱፐር ስፖርት ስፖርትን በአፍሪካና በአለም ደረጃ ከማስተዋወቅ አንጻር ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ እንደ ክልል የመጀመሪያ የሆነው ቢሮ በሀዋሳ በመክፈቱ እጅግ ተደስተናል ብለዋል።

አቶ በየነ ስፖርት በህዝብ መካከል መተሳሰብንና አንድነትን የሚያመጣ መሆኑን ገልጸው የተጀመሩ ልማቶችን ለማስቀጠልም ሆነ የነዋሪውን፣ የሲዳማ ህዝብን ባህልና እሴትን ለማስተዋወቅ ምቹ እድል የሚፈጥር ነውም ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም እግር ኳስ በ11 ተጫዋቾች ተባብረው ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸው የተለያዩ ክልሎች ተጋግዘውና ተባብረው ከሰሩ ሀገርን በቀላሉ ማሳደግ እንደሚቻል ማሳያ ነውም ብለዋል አቶ በየነ።

የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል ቱ/ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጀጎ አገኘሁ የስፖርት እንዳስትሪው በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እድገትና ሁለገብ እቅዶቻችን ላይ ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አቶ ጀጎ አክለውም መንግስት ለዘርፉ ትኩረት እንደሰጠው ገልጸው ይህ ስመ ጥር ሱፐርስፖርት በሐዋሳ ከተማ መጥቶ በጋራ እንድንሰራ እድሉን ስላገኘን ተገቢውን ድጋፍም የምናደርግ ይሆናል ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ እና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ሚልክያስ ብትሬ የሐዋሳ ከተማ ለእንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ መሆኗን ገልጸው ለአምባሳደርነትም የሲዳማ ቡናና የሐዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ መቀመጫ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

የሐዋሳ ከተማ እንደ ሀገርም ስመ ጥር የሆኑ በርካታ ተጫዋችን ማፍራት የቻለች መሆኑን የተናገሩት አቶ ሚልክያስ በ2013 ዓ/ም ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ኘሪሜርሊግ እግር ኳስ ውድድር በዲኤስቲቪ መታየት ደግሞ ብዙ ለውጦች የታየበት ነው ብለዋል።

መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ያደረገው ዲኤስቲቪ በሐዋሳ ቅርንጫፍ መከፈቱ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር ለወጣቶች የሚፈጥረው የስራ እድል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን የተናገሩት የዲኤስቲቪ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ገሊላ ገ/ ሚካኤል ናቸው።

ወ/ሮ ገሊላ ድርጅቱ ለሐዋሳ ከተማ በተክኖሎጂ፣ በቱሪዝም እና በሌሎችም ዘርፎች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለም ተናግረዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ጥቅምት 7/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post