በዛሬው ዕለት የደቡብ ኮሪያ ዘመናዊ የመሬት መረጃ አስተዳደር ስርዓት ከፍተኛ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ከሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ጋር በከተማው የመሬት አስተዳደር ስርዓትን ከማዘመን አንፃር ተወያይተዋል።
በኢትዮጲያ 4 ከተሞች ላይ "ኤግዘም" በሚሰኝ የደቡብ ኮሪያ ባንክ አማካኝነት በ30 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚሰራው የመሬት መረጃን ዘመናዊ የሚያደርግ ፕሮጀክት ሐዋሳ ከተማም የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሆነች ተገልጿል።
በቅርቡ የሚጀመረው ዘመናዊው ፕሮጀክት የሲዳማ ክልል የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲ ከፌደራል የመሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት የሚሰራው ሲሆን ለሐዋሳ ከተማ የተሻለ የመሬት አጠቃቀም ስርዓትን በማምጣት ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።
የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከልዑክ ቡድኑ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ ለከተማችን ወሳኝ ሲሆን ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከልና አጠቃላይ ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያሉ መረጃዎችን ከማዘመን አንፃር ጠቃሚ ነው ብለዋል።
መንግስት ካለው ውስን ሀብት ውስጥ አንዱና ዋነኛው መሬት ነው ያሉት ከንቲባው ይህ ሀብት ደግሞ በአግባቡ ተቆጥሮና ተመዝግቦ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የመንግስትን ገቢ መጨመር ስለሚያስችል ይህንን ፕሮጀክት ወደ ከተማችን ይዘው የመጡ አካላትን አመስግነዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ህዳር 02/2014 ዓ/ም
ሐዋሳ