የህዝብ ተቆርቋሪውና ታላቁ የአቶ በሹ ቱሉ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ።

በህዝብ ተቆርቋሪነታቸው እንዲሁም በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ተሳትፏቸው በሲዳማ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያተረፉት የንግዱ ሰው የታላቁ የአቶ በሹ ቱሉ ስርዓተ ቀብር የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲበ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን ጨምሮ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና በርካታ ህዝብ በተገኝበት ዛሬ ነሐሴ/18/2013 ዓም በሐዋሳ ከተማ አላሙራ ሚሽን መካነ መቃብር በክብር ተፈፅሟል።

በሲዳማ ባህል መሰረት ለጀግና እና ክብር ለሚገባው ሰው ብቻ የሚከናወነውን የቄጣላ ስነ ስርዓትን ጨምሮ በፀሎትና በተለየ መንገድ የአስክሬን ሽኝት ተደርጎ በሐዋሳ አላሙራ ሚሽን መካነ መቃብር የታላቁ የአቶ በሹ ቱሉ ስርዓተ ቀብር ተፈፅሟል።

በቀድሞው አርቤጎና ወረዳ ወይም በአሁኑ ቦና ዙሪያ ወረዳ በጎዋቾ ቀበሌ ከአባታቸው አቶ ቱሉ ቃንቁራ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ማሚቴ ቱሉ በ1943 ዓም የተወለዱት አቶ በሹ ቱሉ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሀገር ውስጥና በውጪ ህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ70 ዓመታቸው ነሐሴ/15/2013ዓም ከዚህ ዓለም ተለይተዋል።

በለጋ ዕድሜያቸው የጉሎ ፍሬ በመሸጥ ባጠራቀሟት 35 ሳንቲም ወደ ንግድ ስራ የገቡት ታላቁ የንግድ ሰው አቶ በሹ ቱሉ ከቤተሰባቸው በወረሱት የስራ ፍቅር እና ትጋት ከምንም ተነስተው ታላቅ የንግድ ሰው ለመሆንም በቅተዋል።

በጠንካራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት የሚታወቁት ታማኙ ግብር ከፉይ፣ ለተቸገሩ የሚረዱና ብዙዎችን ለትልቅ ደረጃ ያበቁት አቶ በሹ ቱሉ በተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ ለ600 ሰዎች ቋሚ እንዲሁም ከ1000 በላይ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውንም የህይወት ታሪካቸው ያሳያል።

በህዝብ ተቆርቋሪነታቸው፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው በመላው ሲዳማ ዘንድ የሚታወቁት አቶ በሹ በፖለቲካ ተሳትፏቸው የቀድሞውን የሲዳማ ዞን ወክለው በደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል በመሆን ማገልገላቸውና ለህዝቦች መብት መከበር ትግል ማድረጋቸውም ተገልፅጿል።

ባለትዳር እና የልጆች አባት የነበሩት አቶ በሹ ቱሉ በህይወት ዘመናቸው 9 ወንድና 6 ሴት ልጆችንም አፍርተዋል።

የሐ/ከ/አስ/መ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ነሐሴ18/2013ዓም

ሐዋሳ

Share this Post