የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለመላው የኢትዮጵያ የዲያስፖራ አባላት እንኳን ደህና ወደ ትውልድ ሀገራችሁ በሰላም መጣችሁ ይላል።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ የሆነችው ሐዋሳ ከምንጊዜውም በላቀ መልኩ መላውን የዲያስፖራ አባላትን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቃ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።

በዚህ አጋጣሚም እንግዳ ተቀባይ የሆነው የከተማዋ ነዋሪ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ወደ ሀገሩ እየመጣ ላለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የዲያስፖራ አባላትን የከተማዋ አስተዳደር እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት ይወዳል።

ከተማችን ፍፁም ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ ሆና ጎብኚዎቿን እየተጠባበቀች ስለመገኘቷም የሚገልፀው አስተዳደሩ የዲያስፖራው ቆይታ በከተማዋ ያማረ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለው።

የበርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት የሆነችው ከተማችን ሐዋሳ ጎብኚው እንደየምርጫው እና ፍላጎቱ በቆይታው የማይረሳ ትውስታ ሰንቆ በእናት ሀገሩ እንዲኮራ የሚያስችሉት ናቸው ብለን መናገር እንችላለን።

ከመዲናችን አዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ከተማችን ሐዋሳ በማንኛውም መልኩ ጎብኚው ባሉት የትራንስፖርት አማራጮች ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ በመምጣት ፍላጎቱን ማሳካት እንዲችል ምቹ አጋጣሚዎች ስለመኖሩም አስተዳደሩ መግለፅ ይወዳል።

የዲያስፖራው አባላት በከተማዋ ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችሉትንም አማራጮች በተገቢው መልኩ ስለማዘጋጀቱ የሚገልፀው አስተዳደሩ በዚህ ረገድ አስፈላጊው የመሰረተ ልማት የተሟሉላቸው መሬቶች ስለመዘጋጀታቸው በመጠቆም ጭምር ነው።

ለእንግዶቿ ፍፁም ዘመናዊ እና ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸው የመስተንግዶ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በተመሳሳይ መልኩም እንግዶቻችንን ለመቀበል ዝግጅታቸውን አጠናቀው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

በየትኛውም አቅጣጫ በከተማዋ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምቹና ተደራሽ የሆኑት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎቻችን ጎብኚው ከማንኛውም እንግልት በፀዳ መልኩ የምርጫውን በማከናወን ቆይታው ያማረ እንዲሆን የተለየ አጋጣሚን የሚፈጥሩለት እንደሚሆንም አስተዳደሩ ሙሉ እምነት አለው።

ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ መዋቅራችንም ለከተማዋ ሰላም እና ደህንነት የተጠናከረ ሚና እንዳለው የሚገልፀው አስተዳደሩ በዚህ ረገድ ጎብኚው ከማንኛውም ስጋት ነፃ ሆኖ በከተማዋ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ዋስትና የሚሰጠው እንደሆነ መናገር ይቻላል።

በመጨረሻም ለመላው የሀገራችን የዲያስፖራ አባላት በድጋሚ እንኳን ወደ ትውልድ ሀገራችሁ በሰላም መጣችሁ የሚለው አስተዳደሩ ቆይታችሁ ያማረ እና የማይረሳ ትውስታ የምትሰንቁበት እንደሚሆን በመተማመን ነው።

መልካም የቆይታ ጊዜ ይሁንላችሁ!!!

Share this Post