የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በወንዶ ገነት ወረዳ በባጃ ፋብሪካ ቀበሌ በ5.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስጀመረው የጤና ጣቢያ ግንባታ በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለፀ።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በወንዶ ገነት ወረዳ በተራራማዋ በባጃ ፋብሪካ ቀበሌ በ5.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ደረጃውን የጠበቀ ጤና ጣቢያ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ለመገንባት በገባው ቃል መሰረት በዛሬው ዕለት ወደ ስራ ገብቷል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ፣ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ እንዲሁም ሌሎች የክልልና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የግንባታ ስራው በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።

በወቅቱ በስፍራው የተገኙ የባጃ ፋብሪካ ቀበሌ ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ያስጀመረው የጤና ጣቢያ ግንባታ በአካባቢው የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ምንም አይነት ተቋም ባለመኖሩ ያጋጥማቸው የነበሩ የጤና ችግሮችን የሚቀርፍ በመሆኑ የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልፀዋል።

ነዋሪዎቹ አያይዘውም አስተዳደሩ በገባው ቃል መሰረት የጀመረው ግንባታ በአካባቢው የጤና ተቋም እና የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም የእናቶችን ሞት ከመቀነስ ረገድም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

የግንባታ ስራውን በይፋ ያስጀመሩት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከተማ አስተዳደሩ በወንዶ ገነት ወረዳ በባጃ ፋብሪካ ቀበሌ ከ5.5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስጀመረው የጤና ጣቢያ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልፀዋል።

በከተሞች የተመጣጠነ እድገት እንዲኖርና በመደመር እሳቤ የዜጎችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሐዋሳ ከተማ በዙሪያዋ ያሉ ከተሞችን የመደገፍና የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ የገለፁት ከንቲባው ከባጃ ፋብሪካ ቀበሌ በተጨማሪ በዶሬ ባፈኖ ሐዋሳ ዙሪያ ወረዳ በቃሬሶ ጄላ ቀበሌ እና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ስራ እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል።

በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የተገኙት ዶ/ር ሰላማዊት መንገሻ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ የጤና ጣቢያው መገንባት የጤና አገልግሎትን ከማሻሻልና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የገለፁ ሲሆን ጤና ጣቢያው ደረጃውን ጠብቆ እንዲገነባና ተጠናቆ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል የክልሉ ጤና ቢሮ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/18/2014ዓም

ሐዋሳ

Share this Post