የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት መላውን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሀነ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

በክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር በዋናነት አላማው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በከብቶች በረት መወለዱን በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል ከንቲባው በመልዕክታቸው።

ይህን ታላቅ በዓል መላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሀጢያት ቀንበር ለብዙ ሺህ አመታት ሲማቅቁ ለነበሩ የሰው ልጆች ሁሉ የፈጣሪን ርህራሄ፣ ፍቅር እና አዛኝነትን በመረዳት ስለመሆኑ ያስታወሱት ከንቲባው በዚህም አንዱ ስለ ሁሉም ፅድቅ ሆኖ ይታይ ዘንድ በመቀበል እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህ ፍቅርን ሊሰብክ፣ ደህንነትን ለሰው ልጆች ለመስጠት የመጣው ክርስቶስ በመላው ቤተልሔም ሕዝብ ዘንድ የሚቀበለው ባለመገኘቱ እና በወቅቱ የነበረው ህዝብ በመዘናጋቱ ምክንያት ሁሉም በሩን ዘግቶ በመኛቱ የተነሳ እመቤታችን ድንግል ማርያምም ልጇን የምትወልድበት ሥፍራ እስከማጣት መቸገሯንም ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ ሀይማኖታዊ ዳራውን አስታከው ተናግረዋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን፣ የተዋረዱትን ያከበረ፣ የተለያዩትን አንድ ያደረገ፣ የተበተኑትን የሰበሰበ ክርስቶስ ለአለም መድህን ሊሆን ተወለደ እንደተወለደም ነው ከንቲባው የገለፁት።

እንደ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት እጅጉን የሚልቅ ነው።

በመሆኑም ይላሉ ከንቲባው ይህ በክርስትና አስተምህሮ መሠረት ታላቅ የምስራችን ይዞ የመጣው የክርስቶስ መወለድ በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ ታላቅ በዓል ሆኖ ይከበራል።

ይህን ድንቅ ስጦታ ግን አሉ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ ክርስቶስ የተወለደባት የቤተልሔም ከተማ ከነበሩ ነዋሪዎች ሳይቀር ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ለዚህ ልዩነት መፈጠር ዋነኛው ነገር ብለው ከንቲባው የሚያስቀምጡት ስጦታውን በመቀበልና ባለመቀበል እንዲሁም አብሮ በመሥራትና ባለመሥራት ምክንያት የመጣ ልዩነት እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህ መልኩ የተዘናጉት የቤተልሔም ሰዎች ሳይቀሩ በከተማቸው የዓለምን ታሪክ የሚለውጥ ተአምር እየተሠራ መሆኑን አልተረዱም ነበር።

እኛም እንደ ሀገር ከ2010 ጀምሮ በሀገራችኝ የፈነጠቀውን የለውጥ ብርሀን ልክ እንደ ቤተልሔማውያን በግዴለሽነት ተኝተን፣ በጥቅምና በሽኩቻ ተባልተን፣ በመከፋፈል ተበታትነን፣ በሥልጣን ጥም ሰክረን ያገኘነውን ዕድል በአግባቡ እንዳንጠቀም ብዙ እንቅፋቶች እና መሰናክሎች ተጋርጠውብናል በማለትም አስረድተዋል።

ይህ ታላቅ የሆነው የክርስቶስ ፍቅር በተለይ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ብዙ የሚያስተምረን እንደሚሆን ከንቲባው ተናግረው በዚህም በተለይ ሀገር ለማዳን በሚደረገው ርብርብ ውስጥ አንዳንዱ ተኝቷል፣ ሌላው ምን ያገባኛል በሚል መንፈስና ስሜት ከዳር ቆሟል ጥቂቶቹ ደግሞ በተለኮሰው እሳት ለመሞቅ ተጥደው ይገኛሉ ብለዋል።

አሁን ያለን አማራጭ እንደ ሀገር ለመቀጠል የመጣልንን እድል ተቀብለን ውስጣችን ተኝተው ያሉትን በማንቃት እና በለውጡ ሂደት ብርቱ ተጋድሎ እንዲያደርጉ በማስቻል እንዲሁም ሀገር ለማፍረስ የሚቃጣውን አንድ ሆነን በመመከት ኢትዮጵያን ማስቀጠል ሰንችል ብቻ ነውም ብለዋል ከንቲባው።

እንደኔ እምነት አሉ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን የምናድንበት እና ወደ ታላቅነቷ የምታዘግምበትን እድል ሰጥቶናል።

ይህን እድል ታዲያ ከዳር ለማድረስ ማንቀላፋቱ ይብቃን፣ እጅ መስጠቱን አንልመደው፣ መትጋቱን እንወቅበት እንዲሁም በገጠመን መከራ ልክ ብቻ ባለመመልከት ወደ ታየልን ክብር እንጓዝ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዛሬው ክብር ሊመጣ ካለው ታላቅ ክብር ጋር ሲነፃፀር አንዳችም የሚተካከል አይደለም ያሉት ከንቲባ ፀጋዬ ሁሉም ለሀገሩ የተሰጠ ልዩ ገፀ በረከት እንደሆነ በመገንዘብ ዘብ ይቁም ብለዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ታህሳስ 28/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post