በውይይቱ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ፣ፖሊስ፣ የጸጥታ መምሪያ ኃላፊዎችና የስምንቱም የክ/ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
እንደ ሀገር የገጠመንን ጦርነት እና ሽብር ለመመከት የፀጥታ ሀይሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚያደርጉት ሚና ጉልህ ድርሻ እንዳለው ይታመናል።
ይህን በተለይም እንደ ሐዋሳ ከተማ ያለውን ሰላም እና ፀጥታ ከማረጋገጥ አንፃር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ ነው የከተማዋ ከንቲባ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር የተወያዩት።
በውይይት መድረኩ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ለከተማዋ ሰላም እና ፀጥታ በዘርፉ የተሰማሩ ሀይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ሀገር የማዳን ተልኮ በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ አሉ ከንቲባ ፀጋዬ የፀጥታ ሀይሉ እንደ ሀገር የወጣውን አዋጅ እና መመሪያ ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የተሰጣቸውን ተልዕኮ በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው።
እንደ ከተማ የፀጥታ ስራው በተገቢው መንገድ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን ስለመመራቱ የጠቆሙት ከንቲባው ይበልጥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከዳር ማድረስ ይጠበቃል በማለትም ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ የተስተዋሉ ግድፈቶችንም በፍጥነት በማረም ሊሰራ እንደሚገባም ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ተናግረዋል።
ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ መኒሳ በበኩላቸው የከተማው ነዋሪ መረጃን በአግባቡ በመለዋወጥ በዓላማ አንድነት፣ በቅንጅት፣ በቁርጠኝነት እና በንቃት እያንዳንዱን ተግባር በመፈፀም የከተማዋን ሰላም እና ደህንነት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የከተማውን ጸጥታ ለማስጠበቅ በየክ/ከተማው የሚገኙ ጸጥታ አስከባሪዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ ከወትሮ በተለየ መንገድ ከተማዋን መጠበቅ እንደሚገባም የገለፁት ደግሞ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ናቸው።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የየደረጃው የፀጥታ አካላት በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃትና የውጭ ኃይሎች አሁንም እየተጠቀሙ ያለው የተቀነባበረና የውሸት ፕሮፖጋንዳን ለመመከት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ በተለይም ህብረተሰቡ በተለያዩ አደረጃጀቶች በመታገዝ እያበረከቱ ያለውን ጥረት ለሀገር ህልውና ትልቅ እገዛ እንዳለው አያይዘው ተወያዮቹ ጠቁመዋል።
የከተማዋ ወጣቶች አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እንዲሰሩም ነው የመድረኩ ተሳታፊዎች የገለፁት።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ህዳር 8/2014 ዓም
ሐዋሳ