የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ሰራተኞችና አመራር አካላት "ለሀገሬ ደሜን ለልማት ግብሬን" በሚል መሪ ቃል ለህልውና ዘመቻው የሚውል ድጋፍ አሰባሰቡ።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባልስልጣን ሰራተኞችና አመራር አካላት ለህልውና ዘመቻው 400 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ያሰባሰቡ ሲሆን ደም የመለገስ እንዲሁም የአልባሳት እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ የማበርከት ስራም በዛሬው እለት አከናውነዋል።

ተቋሙ ባካሄደው የደም ልገሳ እና የድጋፍ የማሰባሰብ መርሀ ግብር ወቅት የተገኙት ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሚችል በመዝመት፣ የተለያዩ ድጋፎችን በማበርከት እና አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሀገራዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀው ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብሩን በታማኝነት በቅንነትና በሀቀኝነት የመክፈል ግዴታውን በተገቢው ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አቶ ታምሩ ተፈሪ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባልስልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የተሰባሰበውን ድጋፍ ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ባስረከቡበት የደም ልገሳ መርሀግብር ወቅት የተቋሙ ሰራተኞችና አመራር አካላት ለሀገርህ ህልውና ዝመት፣ ለግስና ጠብቅ በሚል የተላለፈውን ሀገራዊ ጥሪ በመቀበል 400 ሺህ ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ደም የመለገስ እንዲሁም የአልባሳት እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ የማበርከት ስራም ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች የገንዘብ፣ የደም ልገሳና የተለያዩ ድጋፎችን በማበርከት ለመከላከያ ሰራዊት ደጀንነታቸውን ለተጎጂ ወገኖች አጋርነታቸውን በማሳየት ላይ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ታምሩ ተፈሪ ከዚህ ጎን ለጎን ሰራተኞችና አመራር አካላት በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ከስራ ሰዓት ውጪ ጭምር በመስራት የልማት ስራዎችን በተሻለ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት በማከናወን ላይ መሆናቸውንና በዚህም ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጨምረው ገልፀዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ባለን አቅም ሁሉ በመደገፍ አጋርነታችንን እየገለፅን እንገኛለን ያሉት የተቋሙ ሰራተኞች የሀገራቸውን ኢትዮጵያ ህልውና ለማስጠበቅ ደማቸውን እስከመስጠት ድረስ መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁዎች መሆናቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

ግብር ለመክፈል በመጡበት ወቅት በደም ልገሳ መርሀ ግብሩ ላይ የደረሱት ተገልጋይ ወ/ሮ ነፃነት አለሙ እንደ ዜጋ ምዕራባውያን ሀገራችንን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ጥረት ልናወግዝና ልንመክት ይገባል ያሉ ሲሆን ሀገር ለማዳን ዘመቻው እንደ ዜጋ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍ እያደረግን እንገኛለንም ብለዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/17/2014/ዓም

ሐዋሳ

Share this Post