ሆስፒታሉ ዛሬ በክ/ከተማው የ2014 ዓ/ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸምን ከተገልጋዮች ጋር በመሆን ገምግሟል።
ተገልጋዬቹ በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው የመንገድና የመብራት ጥያቄ ችግር አንዲመለስላቸው ጠይቀዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሚልክያስ ብትሬ ሆስፒታሉ በቀደሙት ጊዜያት የነበረበት የግብዓትና ሌሎች ችግሮች በመቅረፉ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
አቶ ሚልክያስ አሁንም እንደ ተግዳሮት የሚጠቀሰው ወደ ሆስፒታሉ የሚያደርስ መንገድ ምቹ አለመሆንና የመብራት ችግርን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የሐዌላ ቱላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራአስኪያጅ አቶ ማራዶና ዘለቀ ሆስፒታሉ ባለው የሰው ሀይል፣ በአደረጃጀቱ፣ ካለው ግብዓት፣ የቀዶ ጥገና እና እየሰጠ ካለው የስፔሻሊቲ አገልግሎት ደረጃውን ወደ አጠቃላይ ሆስፒታልነት ለማሳደግ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ተገልጋዬች ከተለያዩ አጎራባች ወረዳዎች የሚመጡ መሆኑን የገለጹት አቶ ማራዶና ከቀዶ ጥገና ጋር በተያያዘ ከሐዋሳ ከተማ እና ኦሮሚያን ጨምሮ ከተለያዩ ወረዳዎች በሪፈር ወደ ሆስፒታሉ እየመጡ አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙንጣሻ ብርሃኑ ሆስፒታሉ በሚሰጠው አገልግሎት የተሻለ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሲዳማ ክልል መንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ጋር ተወዳድሮ አንደኛ የወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ሙንጣሻ አክለውም የሆስፒታሉ አጠቃላይ ይዘትም በመጀመሪያ ደረጃ ከሚሰጥ አገልግሎት በላይ መሆኑን አስረድተው በየሩብ ዓመቱ በሚደረገው የማይቋረጥ ውይይት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ጥቅምት 12/2014 ዓ/ም
ሐዋሳ