የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ ይህን ያሉት ዛሬ መላው የሲዳማ ህዝብ አሸባሪዎቹ ህወሀት እና ኦነግ ሸኔ እያደረጉ ያለውን ሀገር የማፍረስ ዘመቻን በመቃወም በተጠራው ሰልፍ ላይ ነው።
ህወሀት ላለፉት 27 አመታት ሀገራችንን ዘርፏል፣ ህዝብን ላልተገባ እንግልት እና መከራ ዳርጓል በማለትም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ህወሀት የጦር አውደ ውጊያውን በአማራ እና አፋር መሬቶች ላይ ቢያደርግም የኢትዮጵያን ህልውና በመፃረር መላውን ህዝባችንን የደፈረ እንደሆነም አቶ ደስታ አስረድተዋል።
ይህ የህልውና ዘመቻችን የኢትዮጵያ ህዝብን ይበልጥ አንድነቱን የሚያጠናክረው እንጂ የሚያዳክመው አይሆንም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም መላው የሀገራችን ህዝቦች ከጫፍ ጫፍ በመነሳት እየመከቱት ይገኛሉ ብለዋል።
ሁለቱ አሸባሪ ሀይሎች የእነርሱን ፍላጎት ከሚያራምዱ የውጭ ሀይሎች እና ሚዲያዎች ጋርም በመቀናጀት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ጥለዋል።
የሲዳማ ህዝብ በተለይ በህወሀት የአገዛዝ ዘመን ይደርስበት የነበረውን ግፍ እና በደል ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው ያስታወሱ ሲሆን ይህም ታሪክ የማይረሳው ጥቁር ጠባሳ ሆኖ ይዘከራል በማለት አስረድተዋል።
የሲዳማ ህዝብ በለውጡ የተጎናፀፋቸውን አኩሪ ገድሎች ለመቀልበስ ጭምር እየተንቀሳቀሰ ያለውን የህወሀትን ቡድን መላው ህዝባችን ግንባር ድረስ እስከ መዝመት የደረሰ ቁርጠኝነቱን ሊያሳይ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የኩራታችን ምንጭ ናት አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራችን የማንነታችን መገለጫ ነው በማለት የተናገሩት አቶ ደስታ ይህን በአንፀባራቂ መልኩ ለአለም ለማሳየት አሁን የተጀመረው ትግላችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በማለት ተናግረዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ጥቅምት 29/2014 ዓ/ም
ሐዋሳ