የቀድሞ የሲዳማ ዞን ዋና አሰተዳደር አቶ ቃሬ ጫዊቻ በኢፊድሪ ጤና ሚኒሰትር በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች የላቀ አገልግሎት በመስጠት ተሸላሚ ሆኑ

አቶ ቃሬ ጫዊቻ በሲዳማ ክልል፣ በንሳ ወረዳ፣ ሁንዳርባ መንደር ነው የተወለዱት፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከሁለተኛ ክፍል ጀምሮ የጀመሩት አቶ ቃሬ ጫዊቻ ከ2ኛ እስከ 8ኛ ድረስ ያለውን ትምህርታቸውን በወርቃ፣ በአሎ እና በቤንሳ ዳየ ት/ቤቶች የተከታተሉ ሲሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በዶዶላ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ አቶ ቃሬ እ.ኤ.አ በ1997 ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በነርሲንግ ዲፕሎማ፣ እ.ኤ.አ በ2002 በህብረተሰብ ጤና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በቢ.ኤስ.ሲ እና እ.ኤ.አ እንዲሁም በ2012 ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በልማት ማኔጅመንት ማስተርሳቸውን ይዘዋል፡፡ ከ1997 ጀምሮ ላለፉት 24 ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የጤና ጣቢያ፣ የወረዳ ጤና ጽ/ቤት፣ የከተማ አስተዳደር የአቅም ግንባታ ጽ/ቤት፣ የክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን የአካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነውም ማገልገላቸውም ይታወቃል፡፡ አቶ ቃሬ በጤናው ዘርፍ ባደረጉት አስተዋጽኦ በአገር ውስጥና በዓለማቀፍ ተቋማት ደረጃ የእውቅና ሽልማቶችን እና የምስክር ወረቀቶችን የተቀበሉም ናቸው፡፡ አቶ ቃሬ ጫዊቻ በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ያተኮሩ ችግር ፈች ጥናታዊ ምርምሮችን በማካሄድ ለህትመት አብቅተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ በቢሮ ሃላፊ ማዕረግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ቃሬ ጫዊቻ በዘንድሮው የጤናው ዘርፍ ልማት ዓመታዊ ጉባኤ በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች የላቀ አገልግሎት ያስመዘገቡ ተብለው ተሸላሚ ሆነዋል ፡፡ የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ ጥቅምት 20/2/2014 ዓ/ም ሐዋሳ

Share this Post