የበጋ መስኖ ቅድመ ዝግጅት ስራ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ገለጹ።

የበጋ መስኖ ቅድመ ዝግጅት ስራን በተመለከተ ዛሬ በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ በፍንጫዋና ቱሎ ቀበሌ ጉብኝት ተደርጓል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ኘሮፌሰር ፀጋዬ አርሶአደሩ ከዚህ ቀደም መሬቱን ከሚያከራይበት ሁኔታ ወጥቶ ማምረት በመጀመሩ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከንቲባው ቀበሌያቱ በመገኘት በየክላስተሩ ያለውን የዝግጅት ሁኔታ እና አርሶአደሩ ያለበትን ችግር ተመልክተዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ በቡድን የሚጠቀምበት 21 ሞተር ፓምፕ የተበረከተ ሲሆን ከፍንጫዋና ቱሎ ቀበሌ በተጨማሪ ሌሎችንም ቀበሌያት ያካተተ እንደሚሆን ከንቲባው ተናግረዋል።

አመራሩም ሆነ የግብርና ባለሙያዎች አርሶአደሩን በመደገፍ ላይ ልዩ ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም ከንቲባው አሳስበዋል።

የአርሶ አደሮች የዘር ችግርን ለመፍታትም አስተዳደሩ የ75ሺህ ብር የጥቅል ጎመን ዘር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የሀዌላ ቱላ ክ/ከተማም የ80 ሺህ ብር የዘር ድጋፍ ተደርጓል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ካሱ አሩሳ በበኩላቸው አረሶ አደሩ በምርቱ ትክክለኛ ተጠቃሚ እንዲሆን የገበያ ትስስሩ የተጠናከረ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበባየሁ ላሊማ በበጋ መስኖ የአርሶአደሩን የዝግጅት ሁኔታ መመልከት እና ያለባቸውን ተግዳሮት መፍታት የጉብኝቱ አላማ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶአደሮቹም ከተማ አስተዳደሩ ችግራቸውን በመረዳት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር 24/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post