የባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ በክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር ለአንድ አረጋዊ ያስገነባውን መኖሪያ ቤት በዛሬው እለት አስተላለፈ።

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ በ2013/14 ዓም በክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር አካቶ ጧሪ ለሌላቸውና ለችግር ለተጋለጡ አንድ አረጋዊ ወጣት በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር ያስገነባውን መኖሪያ ቤት በዛሬው እለት አስረክቧል።

ክፍለ ከተማው ሲያካሂድ በቆየው የ2013/14 ዓም የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ መርሀ ግብር ወጣት በጎ ፍቃደኞችን እና የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር አቅም ለሌላቸውና ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች በርካታ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።

በመርህ ግብሩ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ የተመኝ በሽር በክፍለ ከተማው በአንድነት ቀበሌ በአቦ መንደር ለ45 ዓመት የኖሩ ጧሪ የሌላቸው እና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ አረጋዊ ሲሆኑ በአንድነት ቀበሌ በአቦ የሴቶች እድር አባላት ጠንሳሽነት በመንደሩ በሚገኝ በቀበሌ ግቢ ውስጥ የባህል አደራሽ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ባመቻቸው ቦታ የተገነባ አንድ አነስተኛ ክፍል ቤት በዛሬው እለት ግንባታው ተጠናቆ የተረከቡ ሲሆን ለተደረገላቸው በጎነት ለክፍለ ከተማው ፣ ድጋፍ ላደረጉና በግንባታ ስራው ለተሳተፉ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ያላቸውን ከፍተኛ ምስጋና ገልፀዋል።

በርክክብ መርሀግብሩ በዚህ በጎ ተግባር ለተሳተፉ ወጣቶች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለአንድነት ቀበሌ አቦ ሴቶች እድር አባላት ለክፍለ ከተማው አስተዳደር፣ በሰላም ሚንስቴር አማካኝነት በሐዋሳ ከተማ በበጎ ፍቃድ ስራዎች እየተሳተፉ ለሚገኙ ወጣቶች እና ለሌሎች ተባባሪ አካላት የእውቅና ሰርተፍኬት የማበርከት ስራም ተከናውኗል።

የባህል አደራሽ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻላሞ ሳሳሞ በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር ክፍለ ከተማው ባመቻቸው ቦታ በርካታ የክፍለ ከተማው ወጣቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ባላቸው አቅም ሁሉ በመሳተፍ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት በከፍተኛ ተናሳሽነት መሳተፋቸውን የገለፁ ሲሆን ባለን አቅም ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳትና የመተጋገዝ ባህላችንን ልናጎለብት ይገባል በማለት በክረምት ወራት ያደረጉት ተሳትፎ በበጋውም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልፀዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/2/2014/ዓም

ሐዋሳ

Share this Post