የታቦር ክ/ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት የክ/ከተማውን ሰላምና ጸጥታ አጠናክሮ ለማስቀጠል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገለጸ ።

በክፍለተማው ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀበሌ አመራር፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣት አደረጃጀት፣ ገለልተኛ አማካሪዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የታቦር ክ/ከተማ ሰላምና ጸጥታ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ብርሃኑ ዳንኤል፣ የክ/ከተማው ፖሊስ አዛዥ እንስፔክተር መለሰ ኡኑራ እና የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መከላከል ሀላፊ ዋና እንስፔክተር ካሳ ጨቦ በክ/ከተማው የተሻለ ሰላም እንዳለ ገልጸው አልፎ አልፎ የሚስተዋል ትንንሽ የወንጀል ተግባራት መኖሩንም ተናግረዋል።

በክ/ከተማው የስጋት ቀጠናዎች የተለዩ መሆኑን የገለጹት ሀላፊዎቹ በተለይም ጨለማን ተገን በማድረግ፣ የመሰረተ ልማት ችግር ባለባቸው፣ ባልተደፈኑ ቦዮች የሚደረግ የሞባይል ስርቆት መኖሩን አክለዋል።

በክ/ከተማው የሚፈጸሙ ትናንሽ ወንጀሎችን ለመቀነስ ወደህግ የማቅረቡ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ታርጋ የሌላቸው ሞተሮችም ህጋዊ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የክ/ከተማውን የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት ታሳቢ በማድረግ የገለጹት ሀላፊዎቹ ክ/ከተማውን ከጸጥታ ስጋት ነጻ ለማድረግ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ፣ አምፖል በማውጣት፣ ከደንብ አስከባሪ፣ ከቀበሌ ታጣቂ እና ከፓሊስ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት መከላከል ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ አካላትም በአንዳንድ ቦታዎች የሞባይልና ሞተር ስርቆት፣ ነጠቃና የዝርፍያ ተግባርን ለመፈጸም የሚፈልጉ ግለሰቦች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

ተሳታፊዎቹ አክለውም በአንዳንድ በተጠናከሩ መንደሮች በተቀናጀ ስራ ችግሩን ማስቀረት የተቻለ መሆኑን ገልጸው ሁሉም መንደሮችና ብሎክ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ክ/ከተማውን ከስጋት ነጻ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

የሐ/ከ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

መስከረም 29/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post