የኤስ.ኦ.ኤስ ህፃናት መንደር ሐዋሳ ፕሮግራም ኤቢሲዲ ፕሮጀክት ለተጋባዥ እና አጋር ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራትና በአጠቃላይ የትምህርት ቤት መሻሻል ዙሪያ ስልጠና ሰጠ።

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ አቶ ተክሉ አርጋዬ የኤቢሲዲ ፕሮጀክት በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ በሶስት የገጠር ቀበሌያት በአላሙራ፣ በቱሎና በፊንጫዋ ቀበሌያት ከ2184 በላይ ለሚሆኑ ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል።

የትምህርት ጥራት ተደራሽነት እና አጠቃላይ የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮጀክቱ ከሚሰራባቸው መስኮች መካከል አንዱ መሆኑን የገለፁት አቶ ተክሉ በዚህም በክፍለ ከተማው የሚገኙ የቡሹሎ አንደኛ ደረጃ ት/ት ቤት፣ የፊንጫዋ አንደኛ ደረጃ ት/ት ቤት፣ የቱሎ አንደኛ ደረጃ እና የሎቄ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፕሮጀክቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት የሚሆኑ ተግዳሮቶችን በባለሞያ በማስጠናት ክፍተቶችን ከመሙላት አንፅፃር ፕሮጀክቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ነው አስተባባሪው የገለፁት።

የላብራቶሪ፣ የላይብረሪ እና የትምህርት ክፍል ቁሳቁሶችን ማሟላት እንዲሁም ለመምህራን እና ለርዕሰ መምህራን እንዲሁም ለባለ ድርሻ አካላት የግንዛቤ ስልጠናዎችን መስጠት በፕሮጀክቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም በመግለፅ።

ከዚህ በተጨማሪ ሰባት መቶ ሺህ ብር የወጣበት የተማሪዎች መፀዳጃ ቤት በሁለት ትምህርት ቤቶች ማስገንባት እንደተቻለ የገለፁት አቶ ተክሉ ስልጠናውም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ስልጠና የሰጡት አቶ ዘሪሁን መለሰ የትምህርት ጉዳዮች አማካሪ ስልጠናው በከተማው ከሚገኙ 11ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ከ70 በላይ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ም/ርዕሰ መምህራን በትምህርት ጥራት እንዲሁም በአጠቃላይ የትምህርት ቤት መሻሻል ዙሪያ መሰጠቱንም ገልፀዋል።

ለትምህርት ጥራት መሻሻል የትምህርት ቤት የርዕሰ መምህራን ም/ርዕሰ መምህራንና የትምህርት ማህበረሰብ ሚና የጎላ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ገልፀው ከዚህ አኳያ የስልጠናው ሚና የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል።

የትምህርት ጥራት ተደራሽነት የሁሉንም ማህበረሰብ ተሳትፎ ይጠይቃል ለዚህ ደግሞ የግንዛቤ ማስፋት ስራ ውሳኝነት እንዳለው የገለፁት ሰልጣኙቹ የስልጠናው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም አመላክተዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት አቶ ሰሙንጉስ አስቻለው የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ት/ት መምሪያ ተወካይ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ የትምህርት ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልፀዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/16/2014

ሐዋሳ

Share this Post