የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ 1496ኛው የነብዩ መሐመድ የልደት በዓልን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል

ከሁሉ አስቀድሜ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1496ኛው ለታላቁ የመውሊድ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ!

ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያ፣ የእስልምና፣ የክርስትና እና የሌሎችም ነባር እምነቶች ሀገር ናት።

ይህም ብቻ ሳይሆን ህዝቦቿ፣ በእምነቶቻቸው የማይደራደሩባት እና በነጻነታቸውም ቀልድ የማያቁባት ምድር ናት።

መውሊድ የአላህን ቁርዐን ለሰው ልጆች ያወጁት፣ የታላቁ የእስልምና ነቢይ የሆኑት ነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል ነው፡፡

ይህ ታላቅ ቀን፣ በመላው አለም በሚገኙ ሙስሊሞች እና በወገኖቻቸው ሁሉ በድምቀት ይከበራል፡፡

ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን፣ የነቢዩ መሐመድን (ሰዐወ) ልደት ስናከብር ሀገራችን ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ከፍተኛ ጫና እያደረሱባት ባለበት ሰዓት ነው።

ይህም ያሰብነውን የብልፅግና ጉዟችን አልጋ በአልጋ እንዳይሆን እንቅልፍ አጥተው እኚህ ጠላቶቻችን እየተዋደቁ ይገኛሉ።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የሀገራችን ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች እና ሌሎችም እንደተለመደው እጅ ለእጅ ተያይዘን ፈተናዎቻችንን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ዕድል በኢትዮጵያውን እጅ እንዳለ በፍጹም እናምናለን፡፡

ከመውሊድ በዓላችን የምንማረው ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) በመካ ተወልደው ሲያስተምሩ፤ የተቀበሏቸው ጥቂት፣ የተቃወሟቸው ብዙ እንደነበሩ ጭምር ነው።

እርሳቸው ያመጡትን ለውጥ ለማስቀረት ብዙ ተደክሟል። በጽናት፣ በተጋድሎና በጊዜ ውስጥ ግን ብዙዎች ከጎናቸው ቆመዋል። የኛም የለውጥ ጉዞ እንዲሁ ነው።

በቆየው ኢትዮጵያዊ የመተዛዘን እና የመረዳዳት ባሕል ታላቁን የመውሊድ በዓል፣ በገጠመን አስከፊው የህልውና ዘመቻችን ምክንያት ከሚኖሩበት ተፈናቅለው፣ በየቦታው የተጠለሉ ወገኖቻችንን በማስታወስ እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

በዚህም ስንበላና ስንጠጣ፣ የሚበሉት የሚጠጡት የሌላቸው፣ ያዘኑ፣የተቸገሩ፣ ብዙዎች እንዳሉ ባለመዘንጋት እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

ፍቅር ከሁሉ ነገር ይበልጣል፡፡ መተሳሰብ እና መደጋገፍ ታላቅ ወንዝ፣ ታላቅ ፈተናን ያሻግራል፡፡ ችግር የጊዜ ጉዳይ ነው።

በድጋሚ ሁላችንንም እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሰን! እንኳን አደረሳችሁ!

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ጥቅምት 07/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post