የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በመሀል ከተማ ክፍለ ከተማ በታላቅ ድምቀት በተከበረበት ወቅት ነው።

አቶ አዲሱ ዱራሞ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የበዓሉን አከባበር በንግግር ባስጀመሩበት ወቅት 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሲዳማ ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ካገኘ ወዲህ በክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበር መሆኑ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀው ሲዳማ በክልል ከተደራጀ ወዲህ ክልሉ የብሔር ብሔረሰቦች ወንድማማችነት እና አንድነት ይበልጥ የጎለበተበት ለሌሎች ምሳሌ መሆን የቻለ ክልል መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

አቶ ትንሳዬ መሳይ የመሀል ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸው "ወንድማማችነት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ ያለው 16ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሲዳማ ብሔራዊ ክልል ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበር መሆኑ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።

አቶ ትንሳዬ አያይዘውም ሀገራችን ኢትዮጵያ በህወሓት የሽብር ቡድን የጥፋት አጀንዳ ተገዳ በገባችበት ጦርነት በቆራጡ ጠቅላይ ሚንስትር በክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት፣ በብሔር ብሔረሰቦች አንድነትና በመላው ኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ድል እየተጎናፀፍን ባለንበት በአሁኑ ወቅት መከበሩ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገውም ጨምረው ገልፀዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተማሪዎች የህገ መንግስት የጥያቄና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ለተሳተፉ ተማሪዎች የክልሉን ህገ መንግስት የያዘ መፅሀፍ በሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ህዳር/22/2014ዓም

ሐዋሳ

Share this Post