የ2014 ዓም የመስቀል ደመራ በዓል በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሐዋሳ ከተማ በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሐዋሳ ከተማ እንደወትሮው ሁሉ በታላቅ ድምቀት በተከበረው የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሀፊ እና የሲዳማ ክልል፣ የጌዲዮ ዞን፣ አማሮና ቡርጂ ልዩ ወረደዎች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፣ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች፣ የበዓሉ ታዳሚዎች፣ የገዳማትና የደብራት የሀይማኖት መሪዎች፣ እንዲሁም የክልል እና የከተማ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በበዓል አከባበሩ ወቅት ባደረጉት ንግግር ዛሬ በዚህ ታላቅ ክብረ-በዓል ላይ ተገኝቼ መልእክት በማስተላለፌ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም እገልፃለሁ ያሉት የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እንኳን ለብረሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጲያ በአለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው የሚይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሀይማኖታዊ በአላት መካከል አንዱ ነው ያሉት ከንቲባው እንደ ሀይማኖቱ አስተምህሮ መስቀል የእርቅ ምልክት እና በአዳም ልጆች እና በአምላክ መካከል የነበረው የጸብ ግርግዳ የፈረሰበት እንዲሁም ጌታችንና መዳኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች በደል ብሎ እራሱን አሳልፎ የሰጠበት በመሆኑም መስቀል ለክርስቲያኖች የደህንነት እና የእርቅ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳልም ብለዋል።

በአይሁዳዊያን የወንጀል ህግ እና እምነት መሰረት መስቀል አመጸኞች ወንጀል ሰርተው ሲገኙ ለዘመናት የሚቀጡበት የፍርድ ማማ እንደነበር ያስታወሱት ክቡር ከንቲባው ነገር ግን ክርስቶስ በምድር ላይ ዞሮ በማስተማሩ በሰንበት እውር በማብራቱ ፣ድውይን በመፈወሱ፣ ጎባጣ በማቅናቱ እና ብዙ ድንቅ ተአምራትን በመስራቱ የሰንበትን ህግ ሽሯል ብለው በቅናት በመነሳሳት ምንም በደል የሌለበትን አምላክ ስለ በደላችን በሁለት ሽፎቶች መካከል በመስቀል እንዲቀጣ አድርገዋልም ብለዋል፡፡

ይሁንና መስቀሉ በአማናዊው የክርስቶስ ደም ነጽቶ የድህነት ምልክት ተደርጎ በመዉሰዱ ያልተደሰቱ የአህዛብ ነገስታት መስቀሉን ቆፍረዉ በመቅበር ለዘመናት የቆሻሻ ክምር ሲቆልሉበት ቢቆይም ንግስት እሊኒ ደመራ አሰደምራ ጭሱ ካረፈበት ተራራ ላይ መስቀሉን አስቆፍራ ለማዉጣት እንደበቃችም ጠቁመዋል።

ከዚህ የምንማረው ኢትዮጵያችን ታላቅነቷና መልካም ነገሯ ተቀብሮ በእላያዪ ለዘመናት የመለያየት፣ የጥላቻና የክፋት ክምር ተቆልሎ ተጭኗት ነበር ያሉት ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ይሁንና እንደክምሩ ብዛት፣ እንደ ሴራው ጥልቀትና እንደ ጥላቻው ክፋት ሳይሆን በአንድነት፣ በመተሳሰብ ፣ በበሳል አመራርና በልጆችዋ መስዋእትነት ታላቅነቷን ከተቀበረበት አውጥተን ወደ ከፍታዋ በማስቀመጥ አሸናፊነቷንና አንጸባራቂ ብርሀኗን በማጉላት ለወዳጇም ሆነ ለጠላቷ ተገቢውን መልእክት የምናስተላልፍበት ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

በተጨማርም ደመራ የሚለዉ ቃል ደመረ አንድ አደረገ የሚለውን ትርጉም እንደመያዙ ዛሬም እኛ ኢትዮጲያዊያን በአንድነት ተደምረንና ተጋምደን በምንፈጥረዉ አንድነት ሀገራችን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ የምንታደግበት ወሳኝ ግዜ በመሆኑ እንደ ችቦ በርተን እንደ ደመራ ተደምረን ሀገርን የመታደግ ሀገራዊ ሀላፊነት ልንወጣ እንደሚገባም ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ገልፀዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

መስከረም/16/2014/ዓም

ሐዋሳ

Share this Post