አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማዋ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ለሚገኙ 410 ስራ አጥ ወጣቶች ነው የመስሪያ ቦታ ያስረከበው።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት በከተማዋ በ2014 በጀት አመት ከ25 ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየት የስራ እድል ለማመቻቸት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለ410 ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው ስራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የማምረቻ ሼድ ማስረከቡንም ነው ከንቲባው ያስረዱት።
በቀጣይም አስተዳደሩ በበጀት አመቱ የያዘውን እቅድ ለማሳካት አስፈላጊውን የፋይናንስና የመስራያ ቦታ የማመቻቸቱን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ከንቲባው የገለፁት።
የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊትም ተገቢው ስልጠናና እና የፋይናንስ አያያዝ አቅም ማጎልበቻ ግንዛቤ የመፍጠር ስራም መውሰዳቸውንም ጭምር ነው ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ያስረዱት።
የስራ እድል የተመቻቸላቸው ወጣቶችም በቀጣይ ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የስራ እድል የሚፈጥሩ እንደሚሆኑ እምነታቸውን የገለፁት ከንቲባው ይህም ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ልማት ያላትን አቅም የሚያጎለብት እንደሚሆን በማስረዳት ነው።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ አቶ ተሰማ ዲማ በበኩላቸው የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለወጣቱ ስራ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎችም ተሞክሮ ሆኖ የሚቀመር ነው ብለዋል።
አስተዳደሩ የፈጠረው የስራ እድል በተለይም በከተማ ግብርና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራ በተለያዩ አምራች ዘርፎች ላይ መሆኑ ውጤቱን ይበልጥ ተጨባጭ ያደርገዋል በማለትም ነው አቶ ተሰማ የተናገሩት።
ለወጣቱ ስራ መፍጠር በሀገር ደረጃ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑንና ሐዋሳ ከተማ ይህንን ተልዕኮ በአግባቡ እየተወጣ ስለመሆኑም አመላካች ነው በማለት ተናግረዋል።
የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዞች ልማት እና የስራ እድል ፈጠራ መምሪያ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ዳሪሞ በበኩላቸው ለወጣቶቹም ይህ ለእናንተ ትልቅ ዕድል በመሆኑ ዕድሉን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ እምርታ ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ለዚህ ስኬትም አስተዳደሩ 30 ሚሊዮን ብር በዕለቱ የማምረቻ ሼድ ለተረከቡ ወጣቶች ብድር እንዳመቻቸላቸውም ነው አቶ ታረቀኝ አያይዘው ያስረዱት።
በዕለቱ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችም አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ያደረገውን ድጋፍ አመስግነዋል።
ወጣቶቹ አያይዘውም የተመቻቸላቸውን እድል ተጠቅመው ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የስራ እድል ለመፍጠርም ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ሚያዝያ 4/2014 ዓ/ም
ሐዋሳ