የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ማሻሻል የሚያስችል ስልጠና ተጀመረ

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር "የተማሪዎችን ሁለንተናዊ ለውጥና ፍላጎት በመረዳት ለተፈጠሩበት ዓላማ የማዘጋጀት ክህሎት" በሚል መሪ ቃል የአሰልጣኞች ስልጠና ነው መስጠት የተጀመረው።

መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና የት/ባለሙያዎች ናቸው ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉት።

የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ም/ሀላፊ የሆኑት አቶ ታፈሰ ገ/ማሪያም ተማሪዎች ችግሮቻቸውን በውይይት መፍታት የሚችሉ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ሲጠቀሙ የሚጠቅማቸውን የሚመርጡ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

የመማር ማስተማሩን ባህል መገንባት እንዲቻል ሀገር በቀሉን ከቴክኖሎጂ ጋር በማገናኘት እራሳቸውን እንዲያበቁ ማገዝ ተገቢ ነው ብለዋል።

መምህራን በሙያ ስነምግባር ብቁ ሆነው በፈጠራ ስራ ክህሎት የዳበሩ ተማሪዎችን ማፍራት ይገባል ብለዋል አቶ ታፈሰ።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ደስታ ዴንኤል ተማሪዎች በመልካም ስነምግባር ታንጸው ለውጤት እንዲበቁ ማስቻል ከሁላችን የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

93 ት/ቤቶች ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደስታ ይህንኑ ወደ ተማሪውና መምህራን በማውረድ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት መስራት ይገባል ብለዋል።

ዶ/ር ሙላቱ በላይነህ በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ሲሆን ስልጠናውን በፍቃዳቸው እየሰጡ እንዳሉ ተናግረዋል።

በሙያቸው የትዳርና የቤተሰብ አማካሪ የሆኑቶት ዶ/ር ሙላት ከጻፉት 7 መጽሀፍት ውስጥ ዛሬ ስልጠና የሚሰጡበት 4ኛው መጽሀፍ ሲሆን በተግባር አልህቆት ላይ የተዘጋጀ ነው።

ከ7_12ኛ ክፍለ ባሉ ተማሪዎች ላይ መሰራት አለበት ያሉት ዶ/ር ሙላቱ በዚህ ዕድሜ ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ፣ የማንነት ጥያቄ እንዲመለስ፣ ማህበራዊ ጉዳያቸው ጤናማ እንዲሆን እና የተሻለ ተግባቦትን እንዲያዳብሩ ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህም መምህራንና ወላጆች ላይ መስራት ለልጆች ለውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የናታን የጋብቻና ቤተሰብ ማማከር ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደሮ ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ስልጠና ከሰኔ 14_17/2014 ዓ/ም የሚቆይ መሆኑም ታውቋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ሰኔ 14/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post