የፅዳት፣ የውበትና፣ የአረንጓዴ ልማት ግንባታ ስራዎችን በማጠናከር ለኑሮ የበለጠ ተስማሚ ከተማ የመፍጠር ስራ በሐዋሳ

ውብ ፅዱና አረንጓዴ ከተማ በመፍጠር ሐዋሳ ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለንግድ፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭና ተስማሚ እንደሆነች ለማስቀጠል የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ።

አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች እንዲሁም መፍትሄ የሚሹ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትና ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት በአጠረ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከወትሮው የተለየ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ገልፀዋል።

ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚረዱ በርካታ የልማት ስራዎች በከተማ አስተዳደሩ በመከናወን ላይ የሚገኙ ሲሆን የዝግጅት ክፍላችን እነዚህን የልማት ስራዎች ተዟዙሮ ተመልክቷል።

ለአብነትም የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የግንባታ ስራው በመፋጠን ላይ ያለው ከመናህሪያ ሼል እስከ ጨፌ የሚወስደው የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ስራ አንዱ ሲሆን ይህ የነዋሪዎች የረዥም ጊዜ ጥያቄ የነበረ አሁን ላይ የግንባታ ስራው በመፋጠን ላይ ያለው ከሼል እስከ ጨፌ የሚወስደው ደረጃውን የጠበቀ የእግረኛ እንዲሁም የብስክሌት መንገድ ጭምር ያለው የአስፓልት መንገድ ግንባታ የምልከታችን አንዱ አካል ነው።

የሐዋሳ ከተማን የቱሪዝም መዳረሻነት ይበልጥ ለማሳደግ ታልሞ በመከናወን ላይ ያለው የሐዋሳ ታቦር ተራራ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ደግሞ ሌላኛው ሲሆን በቅርቡ የዲዛይን ስራው ተጠናቆ የስራ ርክክብ የተደረገበት ወደ ውቢቷ ሐዋሳ ከተማ መግቢያ በር ፕሮጀክት እና ሌሎች ፕሮጀክቶችም እንዲሁ።

ህጋዊነትን በማስፈን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም አለአግባብ የተያዙ መሬቶችን የማስለቀቅና የእግረኛ መንገዶችን የማስከፈት ስራ አካል የሆነውና የግንባታ ስራው በከፍተኛ ፍጠነት በመከናወን ላይ የሚገኝው የእግረኛ መንገድ ከፈታና የመንገድ ጠርዛጠርዝ ልማት ስራ ሌላኛው የአስተዳደሩ የልማት ውጥን አካል ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የአረንጓዴ ልማትና የመንገድ ዳርቻዎችን የማስዋብ እንዲሁም የከተማ ፅዳትና ውበት ጥበቃ ስራዎችም በተጨባጭ በበከናወን ላይ የሚገኙ ናቸው።

የእግረኛ ደህንነት ለማስጠበቅና ለከተማው ተጨማሪ ውበት ለማላበስ ታልሞ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች በመገንባት ላይ ያሉ እግረኞችን ከተሽከርካሪ መለያዎች እንዲሁም ሌሎች ያልተጠቀሱ በርካታ የመሰረተ ልማትና ግንባታ ስራዎችም ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።

እግረኞች በብዛት በሚንቀሳቀሱባቸው የመንገድ ዳርቻዎች የሚቀመጡ ተንቀሳቃሽና ደረጃቸውን የጠበቁ የደረቅ ቆሻሻ መጣያዎች እንዲሁ በመከናወን ላይ የሚገኙ ናቸው።

ታዲያ እነኚህንና ሌሎች ለሐዋሳ ከተማ ተጨማሪ ውበት፣ ፅዳትና አረንጓዴነትን ለሚያላብሱ እንዲሁም ለነዋሪው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለሚሰጡ የግንባታ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅና ዘላቂነት የራሱ የነዋሪው ተሳትፎ፣ ትብብርና ጥበቃ ጉልህ ድርሻ ይጫወታልና የድርሻችሁን ተወጡ የከተማ አስተዳደሩ የዛሬው ቁልፍ መልዕክት ነው።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ሐምሌ/4/2014/ዓም

ሐዋሳ

Share this Post