የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ አብርሃም ማርሻሎ የተመራ የክልሉ የስራ ኃላፊዎችና የግብርና ባለሞያዎች ቡድን በሐዋሳ ከተማ በከተማ ግብርና በመልማት ላይ ያሉ የጓሮ አትክልት ልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን ጉብኝቱ ስራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ድጋፍና የልምድ ልውውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
መላው ህብረተሰባችን በከተማ ግብርና በአነስተኛ ቦታና ቁሳቁሶች የጓሮ አትክልቶችን በማልማት የኑሮ ውድነት ጫናን ሊቀንስ እንደሚገባ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በጉብኝቱ ወቅት ጠቁመዋል።
ህብረተሰባችን ከተለመደው የስራ ሰዓት በላይ በመስራት የስራ ባህሉን መቀየር አለበት ያሉት አቶ አብርሃም የከተማ ግብርና ስራ በንቅናቄ ብቻ የሚሰራ የአንድ ወቅት ስራ መሆን እንደሌለበትና በዘላቂነት የሚተገበር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት ቋሚ ተግባር መሆን እንዳለበትም አክለዋል።
በሲዳማ ብሔራዊ ክልል የሐዋሳ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሱ አሩሳ በበኩላቸው የከተማ ግብርና ስራ ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በስምንቱም ክፍለ ከተሞች ከ33 ሄክታር በላይ ሽፋን ያለው ምርት ማግኘት እንደተቻለ ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም በከተማ ግብርና የጓሮ አትክልቶችን በማልማት የምግብ ወጪን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል ሰርተው ያሳዩ አደረጃጀቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች እንደተጎበኙ የገለፁት አቶ ካሱ ነዋሪዎች ባላቸው ውስን ቦታና ቁሳቁስ የጓሮ አትክልት በማልማት የኑሮ ውድነት ጫናን መቀነስ እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
አስተዳደሩ ለከተማ ግብርና ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ አበባየሁ ላሊማ የሐዋሳ ከተማ ግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው መምሪያው የዘር አቅርቦት፣ የአፈር እና የሞያ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በከተማ ግብርና ስራው በክልሉና በከተማ አስተዳደሩ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አስተባባሪነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች እና ሴቶች ተሳታፊና ተጠቃሚዎች መሆናቸውም ተመላክቷል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ሐምሌ/7/2014/ዓም
ሐዋሳ