'የሲዳማ ክልል እንደ ክልል ከተደራጀ አጭር ጊዜ ቢሆንም አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል''_የፌደራሉ የድጋፍና ክትትል ልዑክ።

መጋቢት 15/2016 ዓ.ም

በአቶ አህመድ ሽዴ የሚመራው የድጋፍና ክትትል ልዑክ የነበረውን የ10 ቀናት ቆይታ በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።

የነበረው ቆይታ በጣም የተሳካ መሆኑን በመግለፅ የሠላም እና የጸጥታ ግምባታ በተመለከተ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሠሩ ሥራዎች ከፍተኛ መሆናቸውን ጠቅሶ ለሌሎች ክልሎችም ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ነው ብሏል።

በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስቶ ክልሉ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለው የሠላም እና የጸጥታ ሥራ በጣም በጥሩ መግባባት ላይ ያለ ሲሆን በአንዳንድ ቀበሌያት /በቁጥር ሦስት የሚሆኑ/ላይ የሚነሱ ትናንሽ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት ያስፈልጋል።

በበጎ አድራጎት ሥራዎች በጣም ጥሩ የተሠራ ሲሆን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በደም ልገሳ አከባቢ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ብሏል ልዑኩ።

አረንጓዴ አሻራ በተመለከተ የተሰሩ ሥራዎች ከ80% በላይ ማሳካት መቻሉን ልዑኩ ያዬ ሲሆን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ለምግብነት የሚያስፈልጉ አትክልቶችን ለይቶ ማዳረስ ያስፈልጋል፤ የተሰሩ ጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።

የግብርና ሥራ በመልካም አፈፃፀም የተገመገመ ሲሆን የግብርና ሥራ የእንስሳት ሀብት ልማትን ጨምሮ እንደ ሀገር ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብሏል ልዑኩ።

ከዚህ በፊት የነበረውን የማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ክፍተት በመቅረፍ አሁን ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ነው ልዑኩ የገመገመው።

የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በክልሉ የተጀመረው ኢንሼቲቭ ሌሎች ክልሎችም መጥተው ልምድ የሚወስዱበት ነው ብሏል።

በቡና ምርትና ምርታማነት ላይ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አመርቂ ነው በመሆኑም የአምራች ማህበረሰብ እና በዚህ ዘርፍ አስመጪ እና ላኪ ሆነው ለሚሰሩ ባለሃብቶች ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ ልቀጥል ይገባል።

በመንገድ ልማት፣በትምህርት ፣ጤና ፣የሥራ ዕድል ፈጠራ ፣የመስኖ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች የሲዳማ ክልል ጠንካራ ውጤት ማስመዝገቡን ልዑኩ ያረጋገጠ ሲሆን የመንግስትና የፓርቲ አደረጃጀቶች ጠንካራ መሆናቸውን ልዑኩ ያረጋገጠ ሲሆን ክልሉ ያለዉን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ከዚህ በላይ እንዲሰራ ልዑኩ አሳስቧል።

በመጨረሻም ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ አጭር ጊዜ ቢሆንም የተመዘገበዉ ውጤት አስደናቂ መሆኑን ነው ልዑኩ የገለፀው ሲል የሲዳማ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል።

Share this Post