መጋቢት15/ 2016 ዓ.ም
ሀዋሳ
የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ ዛሬ ከአመራር አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት በ9 ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ነው የመከሩት።
በዚህ ረገድ አዲስ ለሚገነቡ የቁጠባ ቤቶች የግንባታ ግምት አሰጣጥ ዙሪያ ከንቲባው እና አመራራቸው የመከሩ ሲሆን በሂደቱ ያሉ አሰራሮችን በሚመለከት ያለውን አቅጣጫን አመላክቷል።
በዚህ ረገድ እንደ ከተማ ቀድመው የተጀመሩ 240 የቁጠባ ቤቶችን አስመልክቶም ሊጠናቀቁ በሚገባው ሂደት ላይ ዛሬ የዋለው የአመራሩ የውይይት መድረክ የቀረበውን ጥናት ሰምቶ በተመሳሳይ አቅጣጫ አስቀምጧል።
እንደ ከተማ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ7 አመታት የተቋረጡ የቁጠባ ቤቶች ግንባታ የማስቀጠል ሂደትን በሚመለከት በተጨማሪ በአዲስ መልክ የሚገነቡ የኮንዶሚንየም ቤቶች ግንባታ እና የክፍያን አስመልክቶ ከባንክ አሠራር ጋራ በማገናኘት የቤት ችግር ለመፍታት የሚያስችልም ምክክር አድርጓል።
በዚህም መሠረት አስተዳደሩ የዋጋ ማስተካከያ ላይም ባደረገው ውይይት ባለ አንድ መኝታ 60 ካሬ ጠቅላላ ዋጋ 1 ሚሊዮን 503 ሺህ 337 ብር እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጧል።
በተመሳሳይም የባለ ሁለት መኝታ ቤት ለ75 ካሬ ሜትር ቦታ 1 ሚሊዮን 879 ሺህ 171 መቶ ብር ከ 5ሳንቲም እና ባለ 3 መኝታ 90 ካሬ ጠቅላላ ዋጋ 2 ሚሊዮን 255 ሺህ 005 መቶ ብር ከ8ሳንቲም እንዲሆን በውይይቱ ማመላከት ችሏል።
እንዲሁም የቁጠባና የክፍያ ጊዜን በተመለከተም የከንቲባው መድረክ ለ10/90 ለአራት አመት፣ ለ20/80 አምስት አመት እና ለ40/60 ከ6 እስከ 7 አመት እንዲሆን አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም የማህበር አደረጃጀትን በተመለከተ በስትሪንግ ኮሚቴው በየደረጃው የሚወሰን እንዲሆንም ነው ያመላከተው በውይይት መድረኩ።
እንደ ከተማ ሰው ተኮር የበጎ አድራጎት ስራዎችን በተመለከተም አስተዳደሩ በቀጣይ ወራት በትኩረት ከመስራት አንፃርም የመከረ ሲሆን በውይይቱንም የሁሉም ርብርብ እንደሚገባ ያመላከተ ውሳኔ አስተላልፏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከአላሙራ አካባቢ ጋር በተያያዘ ያለውን ንፁህ የመጠጥ ውሀ ችግር ለመቅረፍ የግንባታ ውሳኔ ላይ በመድረስም ነው የከንቲባዋ የአመራር መድረክ የመከረው።
በቀጣይ እንደ አስተዳደር ሴክተር መስሪያ ቤቶች የ90 ቀናት ዕቅድ በማውጣትና ለተግባራዊነቱ በመትጋት የበኩላቸውን አስተዋፆኦ እንዲነድፉም አቅጣጫ ያስቀመጠው የምክክር መድረኩ ለዚህም እንደ መስተዳድር በትኩረት ይሰራበታልም ብሏል መድረኩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የዘንድሮውን የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ የፊቼ-ጨንበላላ በዓል አከባበር ዙሪያ የመከረው የዛሬው መድረክ በዚህ ረገድ ተገቢውን ኮሚቴ በመሰየምና ወደ ስራ መግባት በሚችልበት አሰራር ዙሪያ አቅጣጫ አስቀምጧል።