"የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና " በሚል መሪ ቃል በሐዋሳ ከተማ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ!!

የውይይቱ ተሳታፊዎች የንግዱ ማህበረሰብ፣ወጣቶች፣ የፍትህ አካላት ፣ በከተማ ውስጥ ያሉ የፌዴራል ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣የሀይማኖት መሪዎች፣የዕድር አመራሮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች በተለያዩ መድረኮች ተሳትፈዋል።

ለየመድረኩ ማህበራዊ መሠረቱን መነሻ ባደረገ መልኩ በክልል እና ከተማ አመራሮች ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ችግራቸውን ለመፍታት መንግሥት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ በመጠቆም በየአደረጃጀቱ ያሉ ባለድርሻዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋልም ተብሏል።

የአካባቢን ሠላምና ጸጥታን በመጠበቁ ረገድም ያለ ወጣቶች ተሳትፎ አስተማማኝ ሠላም ማረጋገጥ ስለማይቻል የአካባቢውንም ሆነ ሀገራዊ ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ወጣቶች ጉልህ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በየወቅቱ የዜጎቿን ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያጎድፉ ሀሳቦች ሠላሟን በማደፍረስ ድብቅ አጀንዳቸውን ለማራመድ የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች እየተፋራረቁ እንደሚገኙ መታወቅ እንደሚገባ ከየመድረኩ ተገልጿል።

ህብረብሔራዊ አንድነትን አለመጠናከር፣ የዜጎችን ሰላም አለማስጠበቅ፣የኑሮ ውድነት ፣ስራ አጥነትና ሌሎችም በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች በመሆናቸው ሚዲያው በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልጿል፡፡

እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች ሚዛናዊና ፍትሓዊ መረጃዎችን በማሰራጨት ለሀገር ሰላም ግንባታ ያላቸው ኃላፊነት በተገቢው መወጣት አለባቸውም ተብሏል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ከመድረኩ የቀረበውን ሰነድ መነሻ በማድረግ በከተማዋም ሆነ በሀገሪቱ የፀጥታ ችግር ምንጭ ናቸው ያሉትን ችግሮችን አንስተው፤ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ፣ የመልካም አስዳደር ችግሮች ለአካባቢው ፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች አንስተዋል በጥልቀት ተወያይተዋል።

በመጨረሻም ሁሉም ህብረተሰብ ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ በሁሉም መስክ የላቀ ሚናውን ሊወጡ እንደሚገባም ተገለጿል።

የዛሬው ውይይት በስድስት መድረኮች የተደረገ ሲሆን የምሁራንን እና የመንግስት ሰራተኞች መድረክን ጨምሮ ቀሪ ማህበራዊ መሠረቶችም ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ግንቦት 4/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post